null Different people are disadvantaged to poor building of Omo-kuraz-one sugar factory.

በኦሞ - ኩራዝ ቁጥር - 1 ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት የተለያዩ አካላት መጎዳታቸውን ገለፁ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፡ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ከጥር 15 – 19 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በኦሞ - ኩራዝ ቁጥር - 1 ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

በቀን 12,000 ኩንታል ስኳር ለማምረት ግንባታው በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በ2006 ዓ.ም ተጠናቆ በ2007 ዓ.ም ወደማምረት ይሸጋገራል ቢባልም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ድክመቶች እስከአሁን ድረስ ለውጤት ሳይበቃ ቆይቷል፡፡

በዚህ ምክንያት መንግስት ፕሮጀክቱን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነጥቆ በተፋጠነ ሁኔታ በ2011 በጀት ዓመት እንዲጠናቀቅ የስራ ተቋራጭ ልየታ ቢያደርግም ከአንድ የቻይና ስራ ተቋራጭ የግንባታ ፕሮፖዛል ከመቅረቡ ባሻገር የተደረገ እንቅስቃሴ እንደሌለ ከዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ካሳ ተስፋዬ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በፕሮጀክቱ መጓተት ከተጎዱ አካላት መካክል አንዱ የስኳር ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ 13,000 ሄክታር መሬት ሸንኮራ አገዳ እያለማ ምርቱ ሲያረጅ እያስወገደ ለአራት ዓመታት በመቆየቱ ስኳር ኮርፖሬሽኑ ለከፍተኛ ኪሳራ እንዲጋለጥ አድርጓል፡፡ በርካታ ሰራተኞችንም ቀጥሮ ያለስራ ደመወዝ በዓመት እስከ ብር 20,000,000 ድረስ በመክፈሉ ለጉዳት ተዳርጓል፡፡

ሌላው ተጎጅ አካል ለፋብሪካው ስራ የተቀጠሩ ሰራተኞች ናቸው፡፡ ከስኳር ምርት ሽያጭ በሚገኝ ትርፍ የዕድገትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ተቋዳሽ ለመሆን ቢያልሙም ከሗላ የተጀመሩ ፋብሪካዎች ግንባታ ተጠናቆ ወደምርት በመሸጋገራቸው ሞራላቸው እንደተጎዳ ከዋና ስራ አስኪያጁም ሆነ ከሰራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ግንዛቤ ለመያዝ ተችሏል፡፡

ለዘመናት ከልማት ርቆ የቆየው አርብቶ አደርም ጭምር ለስኳር ፋብሪካው  ያለማውን ሸንኮራ አገዳ በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያሰበውም አገዳው በማሳው ላይ አርጅቶ ከጥቅም ውጭ በመሆኑ  ካሳ ጠባቂ መሆኑ የተሰማውን ቅሬታ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጿል፡፡

ለፋብሪካው ሰራተኞች ለተለያዩ የአቅርቦት አገልግሎቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶችም ዛሬ ተመርቀው ወደአምራች ኢንዱስትሪ ከመሸጋገር ይልቅ በነበሩት ሁኔታ በመቀጠላቸው እንዳሳሰባቸው ከተደረጉ ውይይቶች ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የፋብሪካው ግንባታ በትክክል በ2011 በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ዋና ስራ አስኪያጁ የመንግስት ውሳኔ በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡

ከተለያዩ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት የፕሮጀክቱ ሰራተኞች የፀጥታ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የህክምና፣ የአምቡላንስ፣ የትራንስፖርትና የመብራት ችግሮች እንዳሉባቸው በማንሳት እንዲፈቱላቸው ኮሚቴውን ጠይቀዋል፡፡ የደቡብ ኦሞ ዞን የሳላ ማጎ ወረዳ አመራሮች ፀጥታን ለማረጋገጥ ከተለያዩ አካላት ጋር በመስራት የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ቢቻልም ችግሩ ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ በየደረጃው ካሉ የመንግስት አካላት ጋር አሁንም በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ለኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

አርብቶ አደሩ በፋብሪካው ግንባታ መጓተት ተስፋ በመቁረጥ ለፕሮጀክቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ወደሗላ እንዳይመለስ ኮሚቴው በተፈጠሩ መድረኮች ማሳሰቢያዎችን አቅርቧል፡፡

ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የተገነቡ ማህበራዊ ተቋማት በተሟላ መልኩ ባይሆንም ወደአገልግሎት መግባታቸው አርብቶ አደሩ በመንደር እንዲሰባሰብ መሰረት በመሆናቸው ኮሚቴው በጠንካራ ጎን የተመለከተው ሲሆን ለሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች የውሃ ምንጭ የሚሆነው የዋና መስኖ ቦይ/ካናል/ ግንባታ ተፋጥኖ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡