null Ethiopian reform cuts corrupt, complex chains away: PM Abiy Ahmed (PhD)

“የሴራ፣ የደባ እና የሽብር ፖለቲካ አስወግደን፤ ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን”

  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጥር 25፣ 2012፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ  ለ5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ጉባዔ በወቅታዊ ጉዳዮች ተንተርሰው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የሴራ፣ የተንኮል፣ የደባ እና የሽብር ፖለቲካ አስወግደን፤ ፈተናውን አልፈን፤ ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን በማለት የመንግስትን ቁርጠኝነት አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት፤ የሴራ ጨወታ ፈታኝ እና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፤ የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠል ሀገረ-መንግስት የማቋቋም እና ተቋማትን የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘው ለውጥ ያለ አንዳች የጥይት ድምፅ እና ኮሽታ መጀመሩን ያወሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ የለውጡን ሂደት ለማጠልሸት የሚደረጉትን ጥረቶች በሞት ሽረት ጥረቶች ለመቋቋም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የብዙ ችግሮች መንስዔ የነበረው ራሱ ገዢው ፓርቲ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል የነበረውን ያልተገባ የጥቅም ሰንሰለት በጣጥሶ ሀገሪቱን ከመስመጥ አደጋ ለመታደግ የተኬደው ርቀት ረዥም እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለውቱን ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅም አልሸሸጉም፡፡

በየቦታው የሚስተዋሉትን ችግሮች በተመለከተም፤ የፌዴራል መንግስት እና የክልል መንግስታት በሕገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ከተወጡ፤ ችግሮች ሳይባባሱ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም የፌዴራል መንግስት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም በማስረጃ አስደግፈው ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ የተማሪዎች እገታ ጋር በተያያዘም፤ መንግስት ባለው መረጃ በእገታ ምክኒያት የሞተ ዜጋ እንደሌለ ገልጸው፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ቡድን ሁኔታውን በቅርበት፣ በአካል እየተከታተለ እንደሆነ እና የተለየ መረጃ ሲኖርም ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ዶ/ር ዐቢይ በአንድ ሀገር ሁለት መንግስት ሊኖር እንደማይችል አስረድተው፤ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የሚደረገውን የሴራ ፖለቲካ በብስለት እና በትዕግስት በማለፍ ሕግን እና ሥርዓትን ለማስፈን መንግስታቸው የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡

የሰላም እጦት እና ያለመረጋጋት ችግሮች እንዴት ይፈታሉ? ለሚለው ጥያቄም፤ መንግስት መሰል ችግሮች በሰላማዊ መንገድ፣ በድርድር፣ በንግግር እና በመሳሰሉት አማራጮች ቢሆን ጥሩ ነው ብሎ እንደሚያምን ጠቁመዋል፡፡ ለዴሞክራሲ እጇን በከፈተች ሀገር ከዚህ ውጭ ያሉት አማራጮች አይበረታቱም ብለዋል፡፡

“ ‘ታስሮ የቆየ ጥጃ’ እና ‘በተዘጋ የፖለቲካ ምኀዳር የኖረ ፖለቲከኛ’ አንድ ናቸው፡፡ ቧርቀው፣ ቧርቀው ቶሎ አይመለሱም፡፡ ሆኖም በነጻነት እና በዝግ ምኀዳር መካከል ያለችውን መካከለኛ ስፍራም ማስተዋል ይገባል” ብለዋል፡፡

በኬኒያ እና በኢትዮጵያ ድንበር በተለይም በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ እና በወረዳው አዋሳኝ የኬኒያ አርብቶ-አደሮች መካከል አልፎ አልፎ ስለሚከሰቱት ግጭቶች ተጠይቀው፤ በጉዳዩ ከኬኒያው አቻቸው ጋር እንደመከሩበት ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የችግሩ ዋነኛ መንስዔ በኢትዮጵያ በኩል የልማት መርኃ-ግብር ተነድፎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖራቸው እና ተመሳሳይ ተቋማት በኬኒያ በኩል አለመኖራቸው በመሆኑ፤ ችግሩ በልማት ምላሽ እንደሚፈታ ዕምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ከማዛወር አኳያም፤ በቅርቡ በመንግስት በኩል የተወሰኑት ውሳኔዎች ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግስታት ለ20 ዓመታት ያህል ያከናወኑት አካል እንጂ፤ አዲስ አሠራር አለመሆኑንም ለተከበረው ምክር ቤት እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ አስገንዝበዋል፡፡ ለአብነትም በተጠቀሱት ዓመታት 2 መቶ 87 የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተሸጠው፤ 49 ቢሊየን ብር ገቢ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ተጨማሪ ብድር እንኳን መውሰድ በማትችልበት ደረጃ ደርሳ የነበረ ቢሆንም፤ ከለውጡ በኋላ በተካሄዱት ድርድሮች የሀገሪቱን ብድር ማስቀነስ እና የክፍያ ጊዜያትን ማራዘም ብቻ ሳይሆን፤ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም-አቀፉ የገንዘብ ተቋም ተጨማሪ 3 ቢሊየን ማስፈቀድ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በተፈቀደ የመንግስት በጀት እና የመንግስት በጀት ሳይነካ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን እያከናወነች መሆኗን ያስታወቁት ዶ/ር ዐቢይ፤ በኀዳሴው ግድብ፣ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በመንገድ ግንባታ እና በሌሎችም የመሠረተ-ልማት ዘርፎች ሁሉ፤ የቀድዶ-ሕክምና ያህል አዲስ አሠራሮች በመተግበራቸው፤ ሀገሪቱ ከመስመጥ ተርፋ እያንሠራራች እንደሆነም አብስረዋል፡፡

በ አሥራት አዲሱ

  የምክር ቤት ፀሐፊ