null FAsSC conducted a site visit at Ministry of Foreign Affairs.

የውጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790 እና ማስፈጸሚያ ደንብ በአግባቡ ስራ ላይ ባለመዋሉ ተጠቃሚዎች መብታቸው እንዳልተከበረ ተገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በስሩ በሚገኙ ተቋማት ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

የመስክ ምልከታው የተካሄደው የውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ተቋም፣ የቆንስላ አገልግሎት ጽ/ቤት፣ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች ነው፡፡

የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ተቋምን በሚመለከት ተቋሙ ከዚህ በፊት በተሰጠው አስተያየት መሰረት የውጭ ግንኙነት እና አገራዊ የደህንነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ የነበረውን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ፣ የራሱን የአሰራር ነጻነት እንዲያገኝ መቋቋሚያ ደንብ ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ እንዲሁም የስርአተ ትምህርት ዝግጅት እና ቤተ-መጽሐፍትና የኮምፒውተር ክፍሉን ለማጠናከር ጥረት መደረጉ በጥንካሬ ከተነሱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

የቋንቋ ላብራቶሪ ዝግጅት፣ የውጭ ግንኙነት አዋጅ ደንብና መመሪያ ተግባራዊ አለመደረጉና የሰልጣኞች ጥያቄ በአግባቡ አለመመለስ፣ ምዝገባና ፈተና በየክልሎች አማካኝ ቦታ  መሆን ሲገባው በአዲስ አበባ ብቻ መወሰኑ ሩቅ ቦታ የሚገኙ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ ችግር መፍጠሩ፣ የትርፍ ሰአት ክፍያ አለመክፈል፣ ከፍተኛ አመራሩ  ለማሰልጠኛ ተቋሙ የሚያደርገው ድጋፍ አነስተኛ መሆንና የቅንጅት ችግር ሊታረሙ የሚገባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የቆንስላ አገልግሎት ጽ/ቤትን በሚመለከት በሰራተኞችና በተቋሙ ሃላፊዎች ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት መኖር፣ የውጭ ተገልጋዮች የአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱ እና የመረጃ ልውውጥ በውስጥ የመረጃ መረብ መያያዙና  በአንድ ቦታ ሁሉም አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ በጥንካሬ ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩል በየስራ ክፍሎች ያለው የሰው ሃይል እና ተገልጋዮች ቁጥር የተመጣጠነ አለመሆን፣ ስራዎች ከሌሎች የሚሲዮን ተቋማት ጋር አውቶሜት አለመደረጋቸው የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የበታች ሰራተኞችና አመራሩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የሚወያዩበት መድረክ አለመኖርና ተቋሙ አድራሻውን ሲቀይር አድራሻውን በመገናኛ ብዙሃን አለመግለጹ በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው በእጥረት  ተነስቷል፡፡

የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋምን አስመልክቶ በማቋቋሚያ ደንቡ መሰረት ቦርድ እንዲቋቋም በተደረገው ድጋፍ ውጤት ማምጣቱ፣ የተለያዩ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ የጥናት ጽሁፍ በማውጣት ተደራሽ ማድረግ እና የጽሁፍ ይዘት የተሻለ እንዲሆን አጋዥ አካላት ጋር ተባብሮ መስራቱና በጎ ምላሽ እያገኘ መምጣቱ እንዲሁም የተቋሙን አዳዲስ መዋቅሮች በማጥናት የሰው ሃይል ለማሟላት ጥረት መደረጉ በጥንካሬ ታይቷል፡፡ ተቋሙ  ለሃገራችን ወሳኝ በመሆኑ ራሱን በሰው ሃይል ከማደራጀትና ከማጠናከር፣ በጀትን በአግባቡ ከመጠቀምና በዋና ኦዲተር በማስመርመር እና ከችግሩ ለመውጣት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎችን በሚመለከት ደግሞ ባለው የሰው ሃይል ሰፊ ስራዎችን መሸፈን መቻሉና በተቀመጠው የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት የሃገሪቱ ጥቅሞች ለማስከበር እየተሰራ መሆኑ፣ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጠናከር እና አገራዊ ውክልናችንን ለማስፋት የሚደረገው ጥረት እንዲሁም አገራዊ ገጽታ ግንባታና ጥቅሞችን የማስከበር ሁኔታ በጥንካሬ ታይተዋል፡፡

በሌላ በኩል የውጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790 እና ማስፈጸሚያ ደንብ በአግባቡ ስራ ላይ አለማዋልና በዚህም ተጠቃሚዎች መብታቸውን እያገኙ አለመሆኑ፣ ከዋና መስሪያ ቤቱም ሆነ በስሩ የሚገኙ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች የሚሰሩ ሰራተኞች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ ከሂደት ባለፈ በወቅቱ ያለመፍታት በእጥረት ከታዩት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

በአጠቃላይ ሚኒስቴር መስረያ ቤቱ ስምምነቶችን ወደ ምክር ቤት ቀርበው እንዲፀድቁ በማድረግ፣ የወጡ አሰራሮችን፣ አዋጆችና ደንቦችን እንዲሁም መመሪያዎችን ተከትሎ በመፈጸም፣ ዋና ኦዲተር የሰጠውን የሂሳብ ግኝት አስተያየቶች ተቀብሎ የማረም፣ ከበታች ሰራተኞች ጋር የሚገናኝበት የመወያያ መድረክ በማዘጋጀት የሚነሱ ቅሬታዎችን በወቅቱ በመፍታት እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ አሰራር ሊኖር እንደሚገባ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉና በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረ መልሶች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ በአንዳንድ ጉዳዮችም የቋሚ ኮሚቴው እገዛ  እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡