null Following the audit findings, the House approved the recommendations that would enable the whole secters having budget to ensure accountability.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦዲት ግኝትን ተከትሎ በባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የሚያስችለውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጸደቀ፣

ምክር ቤቱ ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 46ኛ መደበኛ ስብሰባው የኦዲት ግኝትን ተከትሎ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዲቻል በመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ የሱፍ እንዳሉት በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በመታገዝ በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር በአብዛኛዎቹ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ያለው የሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም መንግስት ከዘረጋው የአሰራር ስርዓት ያፈነገጠ በመሆኑ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የመንግስትን ግዥና የፋይናንስ ስርዓት ባልተከተለ መልኩ ግዥና ክፍያ መፈጸም፣ መሰብሰብ የሚገባውን የመንግስት ገቢ አለመሰብሰብ፣ የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ አለመውሰድና የጥሬ ገንዘብ ጉድልት የመሳሰሉት ችግሮች መለየታቸውን የጠቆሙት አቶ መሀመድ ለእነዚህ ተደጋጋሚ ችግሮች መፈጠር ዋናው ምክንያት መንግስት የኦዲት ግኝትን ተከትሎ የማስተካካያ እርምጃዎችን በማይወስዱ ኃላፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በማጠቃላያ አስተያየቱ እንዳለው ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በፋይናንስ፣ በንብረት አስተዳደር አጠቃቀምና አወጋገድ ረገድ በሚያሳዩት የሃብት ብክነትና ህግን ያልተከተለ አሰራር በመንግስት በኩል እርምጃ ሊወሰድና ያለአግባብ የተመዘበረም የህዝብና መንግስት ገንዘብ ሊመለስ እንደሚገባ አስገንዝቦ ህግና አሰራርን በጣሱ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ ይገባል ብሏል፡፡

ምክር ቤቱም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥና ለልማት የሚመደበው የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማስቻል የሚረዳ መሆኑን በማረጋገጥ ውሳኔ ሃሳቡን በ2 ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በሌላ ዜና ምክር ቤቱ በውሎው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የ2011 በጀት አመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፣

የተቋሙን ሪፖርት በንባብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ዋና እንባ ጠባቂው ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ እንዳሉት ተቋሙ በበጀት አመቱ ከሰራቸው ቁልፍ ስራዎች አንዱና ዋናው ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ መስራት የሚስችለውን አሰራር መዘርጋትና ማቋቋሚያ አዋጁ እንዲሻሻል ማድረጉ ሲሆን በዚህም በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጀት አመቱ በርካታ ቅሬታዎች መቅረባቸውንና ከእነዚህም ውስጥ የመሬት፣ የመኖሪያ ቤትና የካሳ ክፍያ የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና እንባ ጠባቂው ተቋሙ የመፍትሄ ሃሳብ ቢጠቁምም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ምክረ ሃሳቡን ተቀብለው ለማስተካካል ፍቃደኝነት ባለማሳየታቸው ችግሮቹ እስካሁን የቀጠሉ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ምክር ቤቱ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል፡፡

ተቋሙ በመደበኛ የቁጥጥር ስራው የመንግስት መስሪ ቤቶችና የግል የልማት ድርጅቶች ለዜጎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች፣ የሚከተሏቸውን አሰራሮችና የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች የዜጎችን መብቶች የማይጥሱ መሆናቸውን ሲቆጣጠር መቆየቱን ያነሱት ዋና እንባ ጠባቂው የዜጎች መፈናቀል በተከሰተበት ወቅትም ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ችግሩ በተከሰተባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአካል በመንቀሳቀስ የታዩትን ጉድለቶች ለይቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ተቋሙ የሰራቸው ጥሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም አላሰራ ያሉት የህግ ማእቀፎች ካሉ እንዲሻሻሉ ማድረግና የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ እንዳለበት አስታውሶ የመረጃ ነጻነት አዋጁ አተገባበር ላይ ክፍተት ያለባቸውን አካላት ለይቶ ህዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ እንዳለበትና የተቋሙን ስልጣንና ተግባር በሚመለከት በተለያየ ደረጃ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በስልጠናና ከሚዲያ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ሊፈታ ይገባል ብሏል፡፡