null Government bodies should be held accountable for the lack of access to adequate research road projects.

በቂ ጥናት ለሌላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች በጀት የሚፈቅድ የመንግስት አካል ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ተባለ፣

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ሰብሰባ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከሞጆ-ሐዋሳ እና ከሐዋሳ-ሀገረማርያም እያስገነባ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት አስመልክቶ የፌደራል ዋና ኦዲተር ባቀረበው የኦዲት ግኝት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

በተቋሙ ያለውን የፋናንስ ስርዓት ተገዥነት፣ የካሳ ክፍያ ፍትሃዊነትን፣ ደካማ የሆኑ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ላይ እርምጃ አወሳሰድን፣ የፕሮጅክቶች አዋጭነት ጥናትና የላብራቶሪ ምርመራን እንዲሁም የመንገድ ፕሮጀክት ጥራትና ፍትሃዊነትን የተመከለቱ የውይይት መነሻ ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴው ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የፋናንስ ስርዓትን ተከትለው የእያንዳንዱን ፕሮጀክት ታሪክ በማጥናት ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረባቸውንና የኦዲት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ከተቋሙ አደረጃጀትና አሰራር ጀምሮ የማስተካከያ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ብቻ የአገሪቱን የመንገድ ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻልና የክልሎችን አቅም በማሳደግ በዘርፉ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የወሰን ማስከበር ስራው አሁን ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አቅም በላይ በመሆኑ የመንግስትን እገዛ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ተቋሙ በፕሮጀክት አፈጻጸማቸው ደካማ የሆኑ ስራ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን በፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ የሚያደርገው አንዳንዶቹ ውሳኔዎች የአበዳሪ ተቋማትን ይሁንታ ስለሚጠይቁ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ ብልሹ አሰራርን መዝጋትና ተፈጽሞ ሲገኝም ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል አሰራር እየዘረጋን ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ ህይወት ሞሲሳ በበኩላቸው በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ እንደ አገር የሚስተዋለው ችግር የህብረተሰብ ተሳትፎን ያረጋገጠ ማስተር ፕላን አለመኖር መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ህብረተሰቡ በዲዛይን፣ በግንባታና በመንገድ ጥበቃ ሂደቶች መሳተፍ በሚያስችለው ወጥ በሆነ ሰነድ ለመስራት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡

የካሳ ክፍያ ላይ የነበረው አሰራር እንደ አገር ጉድለት የነበረበት በመሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ያልተገባ ዋጋ ከፍለዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በመሆኑም የካሳ አከፋፈል አዋጁ እነዚህን ችግሮች በሚፈታና በዘላቂነት ማቋቋም በሚያስችል መንገድ እንዲሻሻል እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት መላላት እንደሆነ ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቀጣይ ክልሎች በመንገድ ግንባታ ዘርፍ እንዲሳተፉ ለማስቻል አቅማቸውን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚደረግና የዲዛይን ጥራትን ለማረጋገጥም የቴክኖሎጅ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከተሰጠው ትልቅ ኃላፊነትና ከሚያስተዳድራቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አኳያ የፕሮጀክት አመራሩን ማስተካከልና በተለይ ከካሳ ክፍያ ጋር ያለውን የባለቤትነት ችግር ለመፍታት እንዲቻል በአዋጁ ማሻሻያ ላይ በትኩረት መሳተፍ እንዳለበት ጠቆመው አዳዲስ ፕሮክቶች የቀደመውን እያፈረሱ እንዳይሄዱና የአገሪቱ ሃብት ያለአግባብ እንዳይባክን ተቋሙ የረጅም ጊዜ እቅድ ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡

ተቋሙ ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም የታየበትን አማካሪ መሃንዲስ ተጠያቂ ማድረግ ሲገባው በሌላ ፕሮጀክት ተወዳድሮ እንዲያማክር ያደረገበት አሰራር ግልጽነት የጎደለውና አሳማኝ ባለመሆኑ ምክር ቤቱ የተፈጸመውን ህገ-ወጥ ድርጊት ገምግሞ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል አቶ ገመቹ፡፡

አቶ ገመቹ አክለውም ከዚህ በኋላ በቂ ጥናት የሌላቸው ፕሮጀክቶች ሊቆሙ እንደሚገባና ምክር ቤቱም በጀት እንዲፈቀድላቸው የቀረቡ ፕሮጀክቶች በቂ ጥናት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበው ያለአግባብ በጀት ተፈቀዶም ከሆነ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ የገንዘብ ሚኒስቴርና ፕላን ኮሚሽን ናቸው ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በሰጠው ግብረ-መልስ እንዳለው በአገሪቱ በደቡብ አቅጣጫ በተለይም ከሞጆ-ሐዋሳና ከሐዋሳ-ሀገረማርያም ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ከጊዜ፣ ከጥራትና ከወጪ አኳያ ሲታይ መንግስትን ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረገ መሆኑን አስታውሶ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም ለታየበት አማካሪ መሃንዲስ እድል መስጠቱም ምን ያህል የአሰራር ችግር እንዳለበት የሚያመላክት በመሆኑ ፕሮጀክት የሚሰራው በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን ለአገር ያለው ጠቀሜታ እየታዬ መሆኑን በመገንዘብ አስራሩን ፈጥኖ ሊያስተካክል ይገባል ብሏል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለተጓተቱ ፕሮጀክቶች የሰራው የክለሳ ስርዓት ኦዲት ሲደረግ የገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያን ያልተከተለና ለፋይናንስ ስርዓት ተገዥ አለመሆኑ መረጋገጡን ያስታወሰው ቋሚ ኮሚቴው የካሳ አከፋፈሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ባለመሆኑ ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረ መሆኑና የዲዛይን፣ የመስመር መረጣ፣ የአዋጭነት ጥናትና የአፈር ምርመራ ስራዎች በአግባቡ የማይከናወኑ እንደሆነ በኦዲት በመረጋገጡ ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት አኳያ ችግር እንዳለበት ተገንዝቦ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ሊከተል ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡