null Hon. Speaker: The House has committed for protection of Human Rights in Ethiopia.

ይህ የተገለጸው ክብርት አፈ-ጉባኤዋ በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን የሚመራውን የልዑካን ቡድን ተቀብለው በአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ በነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

በውይይታቸውም የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብቶችንና የዲሞክራሲ ግንባታን ለማጠናከር በህገ መንግስቱ ላይ በግልጽ ማካተቱንና ለእነዚህ መብቶች መከበርም ባለፉት አስርት አመታት በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን ክብርት አፈ-ጉባኤዋ አስታውቀዋል፡፡

አገሪቱ የሰብአዊ መብን መከበርና የዲሞክራሲ ግንባታውን የሚያበረታቱ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፣ በቅርቡም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ከእስር መለቀቃቸው፣ ከተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ክርክር መደረጉንና በተወሰኑ አጀንዳዎች ላይም ስምምነት ላይ መደረሱን ለአብነት ጠቁመዋል፡፡

ም/ቤቱም ራሱን የቻለ የዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብትና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም ከመስራቱም ባሻገር ሃያውም ቋሚ ኮሚቴዎች የራሳቸውን ቼክ ሊስት አዘጋጅተው የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን በዕቅዶቻቸው ውስጥ አካተው በመስራት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡

በህገ መንግስቱ መሰረት የሰብአዊ መብት ተቋማት ተቋቁመው ሚናቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙና ም/ቤቱም ተቋሟቱን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ባለፉት 2 አመታት በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ከም/ቤቱ አባላት የተውጣጣ ቡድን እንዲያጣራ መደረጉንና በምልከታው የተገኘውም ግኝት ለም/ቤቱ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ም/ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ ማሳለፉንም ተናግረዋል፡፡ በውሳኔው መሰረትም ተጠያቂነት ያለው የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ በአገሪቱ ለተፈጠረው መረጋጋት ም/ቤቱ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም አብራርተዋል፡፡

በአገሪቱ ለተጀመረው የሰብአዊ መብት መከበርና የዲሞክራሲ ግንባታ ኮሚሽኑን ጨምሮ ሌሎች አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ የበለጠ ጥንካሬ እንደሚሰጥም ገልፀዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን በበኩላቸው በተደረገው ውይይት ጥሩ ማብራሪያ መሰጠቱና በሰብአዊ መብት ዙሪያ ፓርላማው የሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡