null House endorses re-establishment proclamations for ENA, EPA

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበለትን አዋጅ መርምሮ አጸደቀ፣

ምክር ቤቱ ህዳር 04 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ማቋቋሚያ አዋጆች ለማሻሻል የቀረቡለትን ሁለት ረቂቅ አዋጆች መርምሮ አጸደቀ፣

የምክር ቤቱ አባላት የሁለቱንም ተቋማት ደሞዝና ጥቅማጥቅም አወሳሰንን አስመልክቶ መብራራት ይገባቸዋል ያሉአቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

የረቂቅ አዋጆቹን መሻሻል አስፈላጊነት አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ የተከበሩ አቶ አበበ ጎዴቦ እንዳሉት የድርጅቶቹ ማቋቋሚያ አዋጅ ቀደም ሲል የጸደቀ ቢሆንም ምክር ቤቱ የተቋማቱን አመራሮችና ሰራተኞች ደሞዝና ጥቅማጥቅም ለመወሰን የሚያስችል አሰራር የሌለው በመሆኑ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹ ቦርድ ያላቸው በመሆኑ ከምክር ቤቱ ይልቅ ለቦርዱ ኃላፊነቱን መስጠትና የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ  ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉ ከጊዜና ከአዋጭነት አንፃር ተመራጭ ተደርጎ መወሰዱንም ነው አቶ አበበ የተናገሩት፡፡

ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እስካሁን ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በቀጣይም በሚዲያ ኢንዳስትሪው ውስጥ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደሰግ እንዲችሉ አደረጃጀታቸውን እንዲሁም ደሞዝና ጥቅማ-ጥቅማቸውን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ለማቋቋም ቀደም ሲል የጸደቀው አዋጅ በተለይ የተቋሙን ዋና ስራ አስፈጻሚና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ደሞዝና ጥቅማጥቅም አወሳሰን ላይ  ክፍተት የነበረበት በመሆኑ ይህንን አዋጅ እንዲሻሻል ማድረጉ ችግሩን ይፈታዋል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱም በማሻሻያ ረቂቅ አዋጆቹ ላይ በጥልቀት ከተወያየና ከመረመረ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ10 ተቃውሞ፣ በ10 ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ9 ተቃውሞ፣ 12 ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ የሁለቱም ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ደሞዝና ጥቅማ-ጥቅም በቦርድ እንዲወሰን የሚለውን የረቂቅ አዋጁን ሃሳብ ተቀብሎ አጽድቋል፡፡