null House refers draft Federal Fiscal Budget to committee

ምክር ቤቱ የ2013 ረቂቅ በጀትን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

 

የኢፌዴሪ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው 476 ቢሊየን የፌዴራል መንግስት የ2013 ረቂቅ በጀትን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

 

ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች /ቤት በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ባካሄደው 16 መደበኛ ስብሰባው በገንዘብ ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የፌዴራል መንግስት 2013 ረቂቅ በጀት በተመለከተ በቀረበው የበጀት መግለጫ (Budget Speech) ላይ በስፋት ተወያይቷል፡፡

 

የፌዴራል መንግስት 2013 ረቂቅ የበጀት መግለጫ ያቀረቡት ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ መንግስት ባጋጠመው በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ሳቢያ ተቀዛቅዞ የነበረውን ኢኮኖሚ ለማስተካከል አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ነድፎ በተጠናከረ መልኩ ተስፋ ሰጪ መሻሻሎችን በማምጣጥ ላይ ቢገኝም በለማቀፍ ደረጃ እና በአገሪቱ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ በሀገሪቱ የጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

 

ወረርሽኙ በቀጣይ በጀት አመትም በኢኮኖሚው ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንኑ ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል፡፡

 

ለ2013 በጀት አመት ለካፒታል እና ለብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪያ በጥቅሉ 476 ቢሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡

 

ከዚህ ውስጥ 350 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከዕርዳታ የሚሰበሰብ ሲሆን 126 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለቱን ደግሞ ከውጭ ሀገር ብድር 46 ቢሊየን እና 78 ቢሊየን ብሩን ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱንም ነው ሚንስትሩ የተናገሩት፡፡

 

ለ2013 ተደግፎ የቀረበው የፌደራል መንግስት በጀት ካለፉት የበጀት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር መጠነኛ ጭማሪ እንዳለው አመልክተው በጀቱን ስራ ላይ የሚያውሉ አካላት የመንግስትን የፋይናንስ፣ የግዥ እና የንብረት አስተዳደር ህጎችን ተከትለው ስራ ላይ እንዲያውሉ አክለዋል፡፡

 

ይህንንንም ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ እንዲሁም የተጀመረው ተጠያቂነት የማረጋገጥ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው የጠየቁት፡፡

 

የቀረበውን የ2013 ረቂቅ በጀት አስመልክቶ በምክር አባላት በርከት ያሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፤ በገንዘብ ሚንስትሩ በክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

 

የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በቀረበው የ2013 ረቂቅ በጀት ላይ በየደረጃው ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደሚደረጉና በእነዚያ መድረኮች ላይ ዝርዝር ጥያቄዎችን አቅርቦ መወያየት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የፌዴራል መንግስት የ2013 ረቂቅ በጀት ቁጥር 40/2012 ሆኖ ለዝርዝር ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡