null House rejects a resolution lodged to endorse leaders and MPs placement to standing committees

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን ለማፅደቅ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ውድቅ አደረገ፤

ጥቅምት 27/2011 ዓ.ም፤ ምክር ቤቱ 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን የአካሄደ ሲሆን ፤ ሰፊ ክርክር  በጉባኤው  ተስተውሏል፤ በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው  ይህ መደበኛ ስብሳባ ከወትሮው  በተለየ፤ የሚያስደምም ጥልቅ ክርክር አስተናግዷል፤

ምክር ቤቱ  የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለመወሰን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቅው ቢሆንም፤አመራርና አባላት ምደባን ለማፅደቅ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ግን ሳያፀድቀው ውድቅ አድርጎታል፤

የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል በፀደቀው  የውሳኔ ሃሳብ መሰረት የቋሚ ኮሚቴዎች  ቁጥር ከ20 ወደ 10 ዝቅ ብሏል፤ የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመደቡት የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራር የተከበሩ አቶ አማኑኤል አብርሃም እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመሩ የተመደቡት የተከበሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ከምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

በተለይም  በአቶ አማኑኤል አብርሃም ላይ የምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ትችት ያነሱ ሲሆን፤ ቋሚ ኮሚቴውን ለመምራት በትምህርት ዝግጅትም ሆነ ፤ ያላቸው ልምድና እውቀት በቂ አለመሆኑን  ገልፀዋል፡፡ የመንግስት  ረዳት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ ባሉበት ወቅትም  ምክር ቤቱ ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ ከዳረጉት አመራሮች ማካከል ናቸው  ሲሉ  ምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፤

አቶ ሞቱማ መቃሳ የመከላከያ ሚኒስቴር ሆነው አገልግለው ሲያበቁ  ፤ ተመልሰው በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራር ላይ መመደባቸው፤ ምክር ቤቱ ቦታ ማፈላለጊያ እንደ ሆነ የሚያስመስል ነው የሚል ቅሬታ ከምክር ቤት አባላት አስነስቷል።

ምክር ቤቱ ከአስፈፃሚው አካል ተፅዕኖ መውጣት እንዳለበትና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል  በተለይም የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል መንግስት በቅርቡ የወሰደውን እርምጃ በሚፃረር መልኩ የህግ፤ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመራ የተመደበው አመራር አግባብነት እንደሌለው  የምክር ቤቱ አባላት አበክረው ተቃውመዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው እየተባለ በተደጋጋሚ መተቸት የለበትም፣ ለወከለን ህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ልንሰጥ ይገባል፣ውሳኔወችን ተቀብለን ማጽደቅ ብቻ ሳይሆን ተገቢነት የሌላቸው ውሳኔዎች ለምክር ቤቱ ሲቀርቡ ውድቅ ማድረግ መቻል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ የአመራር እና አባላት ምደባ እንደገና ጥልቅ ውይይት ተደርጎበት መቅረብ እንዳለበትና ብቃት ያለው ሰው በተገቢው ቦታ ላይ በአመራርነት ሊቀመጥ እንደሚገባ ምክር ቤቱ በቀጣይ መወሰን አለበት ተብሏል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ  የተከበሩ  አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤የቋሚ ኮሚቴ የአመራር እና አባላት  ድልደላ በድርጅት ውይይት የተላለፉ ውሳኔዎችን እና የተገኙ ግባቶችን በማጤን መደረጉን ገልፀዋል፤

በመጨረሻም  ውሳኔ ሃሳቡን ለማፅደቅ ሁለት አመራጮች ቀርበው፤

1ኛ.የእያንዳንዱን የቋሚ ኮሚቴ የአመራርና አባላት  ምደባን በተናጠል  በማየት  ለሌላ ቀን ሳይተላለፍ መወሰን፤

2ኛ. እንደገና ጥልቅ ውይይት ተደርጎበትና በአፅንኦት ታይቶ  በሌላ ጊዜ  እንዲቀርብ የሚለው አማራጭ በአብላጫ ድምፅ  ተወስኗል፤

በመሆኑም የቋሚ ኮሚቴ  አመራርና አባላት ምደባን ለማፅደቅ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በቀጣይ ጊዜያት   እንደገና እንዲታይ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ   ውሳኔ አስተላልፏል፡፡