null Human Rights Commission presents performance report to House

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም አዳመጠ

ምክር ቤቱ ዛሬ ጥር 14/5/2012 ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን የ2012 በጀት አመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም አዳመጠ፡፡

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በሪፖርታቸው እንደገለጹት የኮሚሽኑን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አላማ እና ተልእኮ አንጻር በሙሉ ነጻነት እንዲሰራ የማያስችሉ የፖለቲካ አስተዳደር እና ተጽእኖ በመኖሩ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አሁን ተቋሙን በአዲስ መልክ የማዋቀር እና የማደራጀት ስር ነቀል የለውጥ እርምጃዎች የማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም  አንስተዋል፡፡

በሃገራችን  የለውጥ ሂደቱ የገጠሙት ውስብስብ ተግዳሮቶች እና እንቅፋቶች የሰብአዊ መብት ቀውስ እንደፈጠረ ገልጸው ይህም ችግር ከፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሞያዊ ቀውስ የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም የሃገርን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ የሁሉም ዜጎች ድርሻ በመሆኑ የሰብአዊ መብቶችን ከማክበር እና ከማስከበር ረገድ ሁሉም ዜጋ የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመው በኢትዮጵ ዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው የሰብአዊ መብት ጥሰት መንግስት መፍትሄ ሊያበጅ ይገባል ሲሉም አንስተዋል፡፡

ሪፖርቱን አስመልክቶ በምክር ቤቱ ከተነሱት ሃሰብ እና አስተያየቶች ውስጥም ሪፖርቱ ሃገሪቷ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና በተለያዩ አከባቢዎች እየተከሰተ ካለው የሰብአዊ መብት ጥሰት አንጻር በአጥፊዎች ላይ እየተወሰደ ስላለው እርምጃ ኮሚሽኑ አጥፊዎች በህግ ፊት እንዲቀርቡ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን በሪፖርቱ ሊገለጽ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የህግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኮሚሽኑ ያለበትን የአፈጻጸም ደረጃ በሚመለከት ድጋፍ እና ክትትል ሊደረግለት እንደሚገባ ጠቅሶ አዲስ በሚወጡ እና በሚሻሻሉ ህጎች ዙሪያ በሚደረጉ የውይይት መድረኮች ተቋሙ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ በጥንካሬ የሚታይ መሆኑን ገልጾ ሪፖርቱን አስመልክቶ በምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ሃሳብ እና አስተያየቶችን በማካተት በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በሰዎች የመነገድ እና በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አውጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ዘጋቢ:- ለምለም ብዙነህ