null If civil servants were offered for election, it is not possible to continue government work.

የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ እጩነት የሚቀርቡ ከሆነ  በመንግስት ስራ ላይ መቀጠል እንደማይችሉ ተገለጸ፡፡

ሐምሌ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ- ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የአስርጂዎች መድርከ በማዘጋጀት  በረቂቅ ህጉ ላይ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዶ.ር ሲሳይ አለማውና ዶ.ር ጌታቸው አሰፋ የረቂቅ ህጉ  አስረጂዎች ሆነው የቀረቡ  ሲሆኑ ፣ በጉዳዩ ዙሪያም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ረቂቅ ህጉ  ከዚህ በፊት  በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ በርካታ ክፍተቶችን በመሙላት በምርጫው ሂደትና  ውጤት ላይ  የበለጠ ተዓማኒነትን ለመፍጠር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የመንግስት ሰራተኞች በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራቸው በጊዜያዊነት መልቀቅ እንዳለባቸውም ተብራርቷል፡፡

የመንግስት ሰራተኞች ገቢ ከስራቸው  የሚያገኙት ደመወዝ ሆኖ ሳለ በጊዜያዊነት ከስራ ገበታውቸው እንዲለቁ የሚደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው ? የሚል ጥያቄም  ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል፡፡

የመንግስት ሰራተኞች  በስራ ሃላፊነት ያገኙትን ስልጣንና የመንግስትን ሃብትና ንብረት ለምርጫው አገልግሎት እንዳያውሉት  ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ   ተናግረዋል፡፡

የመራጮች መዝገብ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮፒ እንደሚሰጣቸው በረቂቅ ህጉ ላይ የተገለጸ ሲሆን ፣ ይሄ የሆነበት ምክንያትም ተደጋጋሚ መዝገብ ካላ ለማጣራትና የተመዝጋቢዎችን ግልጽነት ለማረጋገጥና ከውጤቱ ጋር ለማገናዘብ  እንዲቻል መሆኑን ወ/ሪት ብርቱካን ገልጸዋል፡፡

የመራጮች ምዝገባ ተገቢነት ላይ ከዚህ በፊት  በርካታ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበርም ወ/ሪት ብርቱካን አክለዋል፡፡

ረቂቅ ህጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች  ምስረታ ጀምሮ  እስከ የመስራች ቁጥር አባላት ድረስ አዳዲስ አሰራሮችን  እንዳካተተ  ተገልጿል፡፡

አንድ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉትም በረቂቅ ህጉ  ተጠቅሷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም በረቂቅ ህጉ ላይ ቢጨመሩና ቢስተካከሉ ያላቸውን አስተያቶች አቅርቧል፡፡

ረቂቅ ህጉ በርካታ ድንጋጌዎችን ያካተተ ሲሆን ፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች  በስነ-ምግባር የሚደግፏቸውን ዜጎች አክብረው ለምርጫ ተወዳድረው አሸናፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ  መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ  ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቸ ቅሬታ ካላቸው በሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ቅሬታውቸውን በየደረጃው ላሉ አካላት ማቅረብ እንዲችሉ እድል የሚሰጥ ረቂቅ ህግ እንደሆነም ወ/ሮ የሺእመቤት አክለዋል፡፡