null Inquiry Board conducted a field inspection.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ በኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያና የህክምና መስጫ ማዕከል የመስክ ምልከታ አካሄደ፡፡

ሚያዚያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት የመስክ ምልከታው ዓላማ በአለም ብሎም በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት ያዘጋጀውን የኮቪድ 19 የህክምና መስጫ ማዕከል የስራ እንቅስቃሴን መቃኘትና በሚያገጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ዘርፉን ከሚመሩት የህክምና ባለሙዎች ጋር በጋራ በመወያየት የሚፈቱበትን አቅጣጫ ለማመላከት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያና የህክምና መስጫ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ናትናኤል በኩረፅዮን እና የስራ ባልደረቦቻቸው የህክምና ማዕከሉ ቫይረሱ በአገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወነ ባለው ተግባራት እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ለቦርዱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ማዕከሉ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ወረርሽኙን ለመከላከልና የሚያስችል ግብረ ሀይል የማቋቋምና ከላይ እስከ ታች ላሉ የህክምና ባለሙዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ስልጠና የመስጠት ተግባራትን መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡

ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ 450 በቫይረሱ የተያዙና የተጠረጠሩ ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ ገብተው የወጡና አሁን ላይ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ 73 ታካሚዎች በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 3 ታካሚዎች በዚሁ ወረሽኝ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውሰው በቀጣይ ጊዜያት የሞት ቁጥርን ለመቀነስ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይሰራልም ብለዋል፡፡

ባለሙያዎችም መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት እስከ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንና በ3 ፈረቃ የ24 ሰዓት የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይም እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

በመንግስትና በጎ ፍቃደኞች አማካኝነት ለባለሙያዎች የመኝታ ክፍሎች፣ የመከላከያ ቁሳቁሶች እየተሟሉ ቢሆንም አሁንም የውሀ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት ዕጥረት እና የላብራቶሪ ውጤት መዘግየት ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎች ለአደጋ ተጋላጭ ሆነው በመስራት ላይ ስለሚገኙ በቀጣይ መንግስት ባለው አቅም ራሳቸውን አግለው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ከፍሎችና ጥቅማጥቅሞችን እንዲያሟላላቸውም ጠይቀዋል፡፡         

የቦርዱ አባላት ለስራ ሀላፊዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ማዕከሉ ምን ያህል ህሙማንን የመቀበል አቅም አለው? የህክምና ማዕከሉ በማህበረሰቡ ውስጥ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ከአካባቢው ማህበረሰቦች የሚነሱ ቅሬታዎች አሉወይ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የማዕከሉ የስራ ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ማዕከሉ ከ700-800 ታካሚዎችን የመቀበል አቅም እንዳለው እና ማዕከሉ በማህበረሰቡ መኖሪያ መካከል ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙዎችን ቤት ልቀቁ የማለት እንዲሁም ቆሻሻ በሚቃጠልበት ወቅት ቅሬታ የማሰማት አዝማሚ መኖሩን ጠቁመው ከህብረተሰቡ ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ችግሮቹ እየተፈቱ መሆኑ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የስራ ሃላፊዎቹ የቦርዱ አባላት የህክምና ማዕከሉ ድረስ በመምጣት በመከናወን ያሉ ተግባራትን መመልከት በመቻላቸው አመስግነው፤ ምልከታው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል፡፡           

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት አገርና የህዝብ አደራን በመሸከም በዚህ የህክምና ማዕከል እስከ የህይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ አገልግሎት ላይ የሚገኙ የህክም እና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች በእጅጉ ሊመሰገኑ የሚገባና የአገር ባለውለታ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ስራው ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ እንዳልሆነና የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከውሀ፣ ከመብራት፣ ከጥቅማትቅም እና ከግብአቶች እጥረት ጋር ተያይዞ የተነሱትን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚፈቱበትን መንገድ ቦርዱ እንደሚያመቻች እና ቦርዱም በየጊዜው አፈፃፀሙንም እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ባለሙያዎች የህክምና አገልግሎቱን በጥንካሬና በከፍተኛ ጥንቃቄ ማከናወንና እንዳለባቸው፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአቱም በማህበረሰቡ ዘንድ ቅሬታን በማይፈጥር መንገድ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡