null Inquiry Board urged public transport response to #COVID-19

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በመናኸሪያዎች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ አሳሰበ፡፡

ሚያዚያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) ቦርዱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የአዋጁን አፈጻፀም አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን እና ከአገር አቋራጭ አውቶብሶች የስራ ሃላፊዎች ጋርም በአዋጁ አፈጻፀም ዙሪ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡ 

በውይይቱ በአዋጁ አፈፃጸም ዙሪያ ለቦርዱ ከሚቀርቡ ጥቆማዎችና አስተያየቶች ውስጥ ከ50% በላይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚነሱ ቅሬታዎች መሆናቸውን ያነሱት የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት በአዋጁና በአዋጁ ማስፈፀሚ መመሪዎች ተግባራዊነትና ከክልሎች ጋር ስላለው ቅንጅታዊ አሰራር ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ አብዲሳ ያደታ ቫይረሱን ለመከላከል መንግስት ያወጣውን አዋጅና መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ባለስልጣኑ 9 አባላት ያሉት ንዑስ ኮሚቴ በማቋቋምና የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም መመሪያውን ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ እና ከክልሎች ጋር ቼክ ሊስት በማዘጋጀት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡    

በሰዎች መካከል የሚፈጠረውን ንኪኪ ለመቀነስ በአገር አቋራጭና በከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት 50% ወይም በግማሽ ተሳፋሪ መሰራቱን የመከታተል፣ በመናኸሪያዎች መግቢና መውጫ መንገደኞች እጅ የማስታጠብ፣ አልኮልና ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸው የመከታተል፣ በአዲስ አባባ ከተማ የሚታየውን የተሽከርካሪዎች ጭንቅንቅ ለመቀነስና የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ፍሰት ለማሳለጥ ሲባል በኮድ 2 መኪኖች ላይ ከሚያዚያ 9 ቀን 2012 ጀምሮ የወጣው መመሪያ ተግባራዊነትን የመከታተል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እስካሁንም 1,000 ሺ ለሚጠጉ ቫይረሱን ለመከላከል በስራ ላይ ለተሰማሩ ኮድ 2 ተሸከርካሪ ላላቸው ህክምና ባለሙዎች፣ ለፀጥታ አስከባሪ ሃይሎች፣ በስማቸው ኮድ 2 ያላቸው የኩላሊት እጥበት ለሚያካሂዱ ግለሰቦች በነጭ ወረቀት ፍቃድ የተሰጠ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩልም ስራው ድንገተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበጀትና የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

የቦርዱ አባላት በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመከላከል ባለስልጣኑ እያከናወነ ያለውን ተግባራት አድንቀው፤ አሁንም የትራንስፖርት እጥረት፣ ለንክኪ ተጋላጭ የሆነ ግፊያና ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ የማስከፈል፣ ኮድ 2 መኪኖች ከተፈቀደላቸው ቀናት ውጭ በመንገድ ላይ የመንቀሳቀስ፣ አገር አቋራጭና መለስተኛ ተሽከርካሪዎች ከመናኸሪያ ውጪ ሰው ጨምሮ የመጫን እና ለመንገደኞች ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ያለመስጠት ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በቀን 100 ተራ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ አገር አቋራጭ አውቶብሶችን በማሰማራት፣ በመናኸሪያዎች ውስጥ ሰዎች እንዳይጋፉና ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቆሙ በቀለም የመቆሚያ ቦታ በማዘጋጀት፣ ለአገር አቋራጭ መንገደኖች በቀን 4 ጊዜ የጉዞ የሰዓት ስምሪትን በማመቻቸት፣  ከመናኸሪያዎች ውጪ የሚጭኑና ከተፈቀደው ጉዞ ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉትን ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ህግን በማስከበር እንዲሁም ለመንገደኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቦርዱ አባላት እና የባለስልጣኑ የስራ ኃላፊዎች በአውቶብስ ተራ በመገኘት ያለውን እንቅስቃሴ ቃኝተዋል፡፡ በመናኸሪው ውስጥ ከሚገኙ የአገር አቋራጭ አውቶብሶች ባለንብረቶች የሽርክና ማህበራት የቦርድ ሰብሳቢዎች ጋር በተወያዩበት ወቅትም ባለንብረቶቹ <<መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲባል አገር አቋራጭ አውቶብሶች ግማሽ መንገደኞችን በእጥፍ ዋጋ እንድንጭን ቢያውጅም በመናኸሪያው ውስጥ 50% ብቻ በመጨመር አንድንጭን እየተገደድን ነው፤ ይህ ደግሞ ባለንብረቶችን ለተለያዩ ኪሳራዎች እያጋለጠን ነው፡፡>> ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ችግሮች እንደነበሩ አሁን ግን በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ መመሪያ ግን የትራንስፖርት ታሪፉ በእጥፍ ክፍያ እንደሆን እንዲሁም ተመላሽ ተሳፋሪ የማያገኙ ተሽከርካሪዎች ከሆኑ ደግሞ እስከ 100% + 50% ማስከፈል እንደሚችሉ መደንገጉን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት በመናኸሪያው ያለው የስራ ሰዓት ስምሪት በአግባቡ መፈጸሙንና ከመጨረሻው የ6፡00 ሰዓት ስምሪት ውጪ ሌላ ስምሪት አለመኖሩን ቦርዱ ማረጋገጡን፣ ታሪፍን በተመለከተ በመመሪው አፈፀጸም ላይ የሚታይ ክፍተት ካለ እንደሚታረም ገልጸዋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለስልጣኑ በቢሮውና በመናኸሪያዎች ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራትን እና ከክልሎች ጋር ቼክ ሊስት በማዘጋጀት በቅንጅት መስራቱን ቦርዱ በጥሩ አፈፃፀም እንደተመለከተው አንስተው፤ ከመንገደኞች ንኪኪ፣ ከታሪፍ ጭማሪና ከህገ-ወጥ ጭነት ጋር ተያይዞ አሁንም ያለተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው ባለስልጣኑ በመናኸሪያዎች ውስጥ የሚያከናቸወናቸውን ተግባራት    የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ