null It has been unable to stop the illegal human trafficking.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን መነሻ በማድረግ የሰጠውን ግብረ መልስ ተግባራዊ ስለመደረጉ ባደረገው የመስክ ምልከታ ገምግሟል፡፡

ለተለያዩ ተግባሮች አፈጻፀም ያመች ዘንድ በየደረጃው ለሚገኙ ፈጻሚዎች የእውቀትና የአመለካከት ስልጠናዎች ቢሰጡም በተገልጋዮች እርካታ ላይ ውስንነት እንዳለ በአስተያየት መልክ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ በምልክታ ወቅት በቀረበው ሪፖርት ተብራርቷል፡፡

የአገር ውስጥ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በዜጎች ላይ ዘመናዊ የባርነት ስርዓት እየፈጸሙ እንደሆነና ለሰራተኞች የሚከፍላቸውም ደመወዝ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከችግሩ አስከፊነት አንጻር ህገ-ወጥ ስደትን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ ማስገደዱን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ በየብስና በባህር የሚያቋርጡ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አገራት ቪዛ ይዘው በአየር መንገድ አማካኝት ወደ ውጭ አገር የሚሰደዱ ዜጎች አስከፊ እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸው በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው ህገ-ወጥ ስራ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ለምን በውጤት የታጀቡ እንዳልሆኑ በቀጣይ በጥልቀት እንደሚፈተሹ አስረድተዋል፡፡

ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ የሚንስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም በበኩላቸው ተቋሙ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ እንደሆነና ችግሩም እስከ ውጭ አገር ድርስ ስር የሰደደ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በተቋሙ የሰው ሀይል ቅጥር ለማሟላት እና ያሉበትን ቁልፍ ችግሮች በየደረጃው ለመቅረፍ ያደረገውን ጥረት በጥንካሬ የተመለከተው ሲሆን በሌላ በኩል ኪራይ ሰብሳቢነትን በመቀነስ፣ በህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ረገድ እና ስራዎችን በቅንጅት መስራትን አስመልክቶ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጦላቸው ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡