null It was noted that it is necessary to create conditions to ensure the peace and security of the community and the protection of the political, social and economic interests of the people.

የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመጠበቅ ምህረት ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ተጠቆመ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ስነ-ስርአት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የአዋጁን አስፈላጊነትና ይዘት በሚመለከት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ የማህበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመጠበቅ፣ በየወቅቱ ለሚከሰቱ ከፍተኛ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት፣ ህግን ለተላለፉ አካላት ምህረት የሚሰጥበትን ሁኔታ በወንጀል ሕግ የተደነገገውን ከህገ-መንግስቱ ጋር በማጣጣም ምህረት የሚሰጥበትን ስነ-ስርአት መደንገግ በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ አራት ክፍሎች እና 16 አንቀፆች ያሉት ሲሆን በየክፍሎቹም የአዋጁ ተፈጻሚነት ወሰን፣ የምህረት ቦርድ ስለማቋቋምና የቦርዱ ስልጣንና ተግባር፣ የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በዋናነት የተካተቱበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በሙስናና በሽብር ጉዳዮች ላይ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት የማጣራት ስራ በደንብ መሰራት ስላለበት በምህረት አዋጁ ውስጥ እንዲካተት የሚሉና ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲባል በዘመቻ የታሰሩት ተጠርጣሪዎችን በማጣራት እንዲፈቱና ምህረቱ ለሁሉም ተፈፃሚ ቢሆን የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ጥያቄዎቹን ሲመልሱ ለሁሉም ይቅርታ ይደረግ የሚለው የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው ወንጀል የሰራ መቀጣት ስላለበት ከወንጀል ነጻ የሆኑትን እና ወንጀል የሰሩትን በማጣራት ተጠያቂ በማድረግ ሃላፊነት ባለው መልኩ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት የመድረኩ አላማ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ አስተያየት ማሰባሰብ መሆኑን እና በውይይቱም ጠቃሚ ግብአት መገኘቱን ጠቁመው በተሰበሰበው አስተያየት መሰረት ቋሚ ኮሚቴው ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በረቂቅ አዋጁ የሚካተቱ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት አካቶ ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት በማቅረብ እንደሚያፀድቅ ገልጸዋል፡፡

ይህ አዋጅ ቀጥሎ ለሚወጣው አዋጅ መነሻ እና አቅጣጫ የሚያሳይ መሆኑንም ጭምር አመልክተዋል፡፡

በመጨረሻም በምህረትና በይቅርታ እንዲሁም ክስ በማቋረጥ ሂደቶች ላይ አልፎ አልፎ የግልጸኝነት መጓደል መኖሩን የሚያሳዩ አዝማሚያዎች መኖራቸውን ጠቁመው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በየደረጃው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡