null Ministry of foreign affairs should strengthen internal audit and solve their findings.

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡

መጋቢት 11 ቀን 2011  ዓ.ም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 ዓ.ም የሂሳብ ኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ በተለያዩ ኤምባሲዎች ውል ሳይታሰር እንዲሁም ከመንግስት የግ¡ አዋጅ ውጭ ያለ ውድደር ከአንድ አቅራቢ የብር 5,953,299.95 የተለያዩ ግዥዎች መፈጸማቸውን እና የፌደራል መንግስት የግዥ መመሪያን በጣሰ መልኩ በጠቅላላ ድምር ብር 1,894,143.5 የተለያዩ የአገልግሎት ግ¡ዎች የተፈጸሙ መሆኑን፣ በሁለተኛ የዲያስፖራ ዝግጅት በሚል የወጣ ወጪ ብር ሰባት ሚሊዮን ማስረጃ ያልቀረበለት መሆኑና ሌሎችንም የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳይ ተነስቷል፡፡

 ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለመሰብሰብ ያደረጉት ጥረት መኖሩንና ለማስተካከል ያላቸው ፍላጎት ጅምሩ ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ ከተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳብ ጋር በተያያዘ ሲያወራርዱ በማስረጃ መሆን እንዳለበት፣ በጀትን በሚመለከት ለታለመለት አላማ ማዋልና የወጡ ወጪዎች በማስረጃ ማስደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ተቋሙ የሂሳብ ሰራተኛው  የጀመረውን የሂሳብ ስራ ሳያጠናቅቅ  የሚያደርገውን የሂሳብ ሰራተኞች ዝውውር  ቢያስተካክል  ችግሮቹ ሊቀንሱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ዩሱፍ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግዥ አፈጻጸም ስርአት፣ የክፍያ አፈጻጸም እና   የተሰብሳቢ ሂሳቦች ሪፖርቶች ትክክለኛነት ላይ  ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደዚሁም የበጀት አጠቃቀም ላይ የአሰራር ስርአት ጥሰት  መታየታቸውን ጠቁመው፤ በኢፌዴሪ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በተዘረጋው የሂሳብ አያያዝና ሂሳብ አወቃቀር ስርአት መሰረት ትክክለኛ፣ ወቅታዊና የተማላ ማስረጃ በማዘጋጀት ለመንግስትና ለልማት አጋሮች የሚቀርበው የመረጃ ጥራት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግም ጠቁመዋል፡፡  የውስጥ ኦዲት አቅምን በማጠናከር በአስቸኳይ ችግሮቹ ታርመው የመንግስት ፋይናንስና የግዥ ንብረት አስተዳደር ህጎች እንዲከበሩ በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር  ብርቱካን አያኖ ከግዥጋር በተያያዘ የተነሱት ችግሮች ከተቋሙ የግዥ መመሪያ ጋር የማይጣጣም  በመሆኑ ማስተካከያ ተደርጎ መፍትሄ የተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብን በሚመለከት የተሰብሳቢና ተከፋይ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን እንዲሁም አንዳንድ ችግሮች የሚፈጠሩት ከክህሎትና ዕውቀት ማነስ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም በመመሪያው መሰረት  በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በሰነዶች ማረጋገጥ የሚፈቱ በመሆናቸው ከቋሚ ኮሚቴውና ከዋና ኦዲተር የተሰጡ አስተያየቶችን ወስደው በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡