null Ministry of science and higher education reported that it has stopped selection of instructors of foreign citizens.

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰቴር የውጭ ሃገራት መምህራን ምልመላ እንደቆመ  ለምክር ቤቱ አሳወቀ፡፡

ሚያዝያ 22/ 2011 ዓ.ም ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ አመት የስራ ዘመኑ በ 37ኛ መደበኛ ስብሰባው በቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው   የተሰማውን ጥልቅ  ሃዘን በመግለጽና የአንድ ደቂቃ የህሊና ፆሎት በማድረግ  የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማሪያም  የውጭ ሃገራት  መምህራን ምልመላ በልዩ ልዩ ምክንያቶች  ከ 2010 ዓ.ም ጀምሮ እንደቆመ ተናግረዋል፡፡

ለተግባራዊነቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በትኩረት  እንደሚሰራ  የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ባቅረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራትን ለማስጠበቅ የህግ ጥሰት ፈጽመው የሚገኙ ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የስነ-ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዳብሮና ውይይት ተደርጎበት ተግባራዊ እንደሆነ ፕሮፌሰር ሂሩት ገልጸዋል፡፡

770 ለሚሆኑ የጎረቤት ሃገራት ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ተሰቷቸው በተለያዩ የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ከስደትና ስደት ተመላሾች መምሪያ በቀረበ የሃገር ውስጥ የስልጠኛ እድል ጥያቄ መሰረት ከኤርትራ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ የተለያዩ ግዛቶች እና ከየመን ለመጡ 809 ስደተኞች በሃገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ምደባ እንደተሰጠ ፕሮፌሰር ሂሩት አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባና ዙሪያው በሚገኙ 167 የግል ከፍተኛ  ተቋማት ካምፓስ / ቅርንጫፍ ማዕከላት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ዳሰሳ   በ46 ተቋማት ላይ ዋና ዋና ችግሮች የታዩ ሲሆን ፤ በዚህም መሰረት ያለ እውቅና ፈቃድ ተማሪ መዝግበው  በማስተማር ላይ የሚገኙ 27 ፣ በርቀት ፈቃድ የመደበኛ እና በመደበኛ ፈቃድ የርቀት በማስተማር ላይ ያሉ 4፣ የእውቅና ፈቃድ ሳያሳድሱ የሚያስተምሩ 6 ፣ ሳያሳዉቁ ህንጻ የቀየሩ 3 ፣ ባልተሠጠ ስያሜ / ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ / የሚጠቀሙ 3 ፣ መረጃ ላለመስጠት ተቋሙን ዘግተው የጠፉ 3 መሆናቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ችግር እንዳለባቸው በተለዩ ተቋማት  ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸው እውቅና እንዴት ሊያገኝ ይችላል የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባል የተነሳ ሲሆን ጉዳዩን ተወያይተን የምናሳውቅ ይሆናል ሲሉ ፕሮፌሰር ሂሩት መልሰዋል፡፡

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  በእቅድ ደረጃ ተይዞ  ወደ ተግባር የተገባበት መሆኑ ፣ ከሃይማኖት አባቶች ፣ አባ ገዳዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰላማዊ የመማር ማስተማር  እስከ ዞን ድረስ እንዲወርድ መሰራቱ ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ  የተመረቁ ተማሪዎች በራሳቸው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መሰራቱ  ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ  በዩኒቨርሲቲዎች በኩል የግብዓት እጥረት መኖሩ ፣ የግዥ ስርዓት መጓተት ፣  የኦዲት ግኝቶችን ለማረም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቃት ያላቸው የተመዘኑ  አሰልጣኞችና  የሰው ሃይል አለሞኖር የሚሉትን ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት ተመልክቷል፡፡

በእጥረት የተዘረዘሩትን አስተያየቶች በግብዓትነት በመውሰድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንዲሰራባቸው የሰው ሃብት ልማትና  ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እምዬ ቢተው አሳስበዋል፡፡