null National Information and Security service in being restructured.

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለውጥ ውስጥ መሆኑን የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ፡፡ የህዝብ አመኔታ የመፍጠር ስራውንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የመስክ ምልከታ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት  ከለውጡ ወዲህ በተቋሙ ስለተከናወኑ የለውጥ ስራዎች የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጀነራል አደም መሐመድና የስራ ባልደረቦቻቸው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የተቋሙን የሰው ሃይል አቅም ለመገንባት፣ አደረጃጀት ለማስተካከል፣ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ንብረት ለመመዝገብ፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስቀረት እና ገለልተኛ ሙያዊ ተቋም ለመገንባት ስለተከናወኑ በርካታ ተግባራት ሃላፊዎቹ ለኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

አገልግሎቱ በሩን ለህዝብ ክፍት በማድረጉ ከህዝቡ በርካታ ጥቆማዎች እየቀረቡለት በጦር መሳሪያ የታገዘ ዘረፋን በማስቆም፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር፣ የቴሌኮም ማጭበርበርንና ሌሎች የሙስና ወንጀሎችን በመከላከል ስኬት መመዝገቡን ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ የተቋሙ በር ለምክር ቤቱም ሆነ ለህዝቡ ክፍት መደረጉ ተቋሙ የለውጡ አካል መሆኑን ጠቁመው ቋሚ ኮሚቴው ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋሙ ግቢ ገብቶ ጉብኝት በማድረግ በመቻሉ ምስጋና ለተቋሙ አቅርበዋል፡፡ ተቋሙ ለህዝብ ሰላምና ፀጥታ እየሰራ ስለመሆኑ ያለማስተዋወቁ ዕጥረቱ መሆኑን በማመልከት የህዝብ ግንኙነት ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ተቋሙ ከዚህ ቀደም ከሚታወቅበት የፖለቲካ ስርዓቱ ተዋናዮች ጠባቂ ከመሆን ወጥቶ ገለልተኛ የሙያ ተቋም ሆኖ በሳይንሳዊ መንገድ የተተነተነ መረጃ ለመንግስት በመስጠት ስጋቶችን አስቀድሞ መከላከል የሚቻል አሰራር ለመዘርጋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉና ህዝቡም ለተቋሙ ከመፍራት ይልቅ ተቀራርቦ እንዲሰራ በማስተዋወቅ በኩል የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ቃል ገብተዋል፡፡

የኮሚቴው አባላትም ተቋሙ የኢትዮጵያን ህዝብ በመደብደብና በመግረፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈፀማቸው በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ወደህግ በማቅረቡ በኩል እንዴት እየሰራ ስለመሆኑ፣ በሚዲያ ይነገር ስለነበረው የመርዝ ጉዳይ፣ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ በመከላከል በኩል ስላሉ ዝግጁነቶች ጥያቄዎች አንስተው በዳሬክተር ጀነራሉና የስራ ባልደረቦቹ ከህግና ከአሰራር ጋር በተያያዘ ስለተሰሩ ስራዎች በማብራራት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡