null Our technology level allows electronic transaction: Ministry

አሁን የደረስንበት የቴክኖሎጅ ደረጃ የኤሌክትሪክ ትራንዛክሽንን ማስጀመር እንደሚችል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስገነዘበ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይና የስራ ባልደረቦቻቸው ይህን ያስገነዘቡት ኤሌክትሪክ ትራንዛክሽን ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰው ሃብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በነበራቸው  ውይይት ወቅት ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የህግ ባለሙያዎች ጋር ሰፊ ጊዜ የፈጀ  ውይይት ሲደረግበት የቆዬ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትሩ በውይይቱም የተገኙ ግብአቶችና አስተያያቶች  የተካተቱበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ተንቀሳቃሽ ስልክንና መሰል መሳሪያዎችን ጨምሮ በኮምፒውተር በመታገዝ የኢንፎርሜሽን መረብ ስራን ማከናወን የሚያስችል እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ንግድንና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚጨምር ቴክኖሎጂ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም አሁን የደረስንበት የቴክኖሎጅ መሰረተ-ልማት ደረጃ የተሟላ ነው ባይባልም ባለን አቅም ጀምረን እያጠናከርን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የረቀቅ አዋጁን ዓላማ አስመልክተውም ሚኒስትሩ ሲያስረዱ ወረቀትንና ኮምፒውተርን ማዕከል ያደረጉ ሰነዶችንና ኢንፎርሜሽኖችን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በእኩል ለማስስተናግድ፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ንግድን ጥቅም ላይ እንድታውልና ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ የዲጂታል ዘመኑን እንድትቀላቀል ለማስቻልና ሁሉን አቀፍ መንግስታዊ ተቋማትን በመገንባት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ህግ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ ለነበሩት የንግድም ይሁን የአገልግሎት ህጎች እውቅና የሚሰጥ እንጅ አዲስ ህግ አለመሆኑን ያስረዱት ሚኒስትሩ  አገራችን ይህንን ቴክኖሎጂ መጠቀሟ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ በዲጂታል ቴክኖሎጅው ውስጥ በመካተት ፈጣን ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ተግባራዊ ሊደረግ ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ረቀቅ አዋጁን አስመልክቶ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች የተሰጠው ማብራሪያ በቂ እንደሆነና ነገር ግን ከተደራሽነትና  ከቋንቋ አጠቃቀም አኳያ ያሉትን ነገሮች በድጋሚ በመፈተሽ የተስተካከለው ሰነድ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲደርሰውና በምክር ቤቱ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ሚኒስቴር መ/ቤቱ  ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት አሳስቧል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው 15ኛ በደበኛ ስብሰባው  ለሰው ሃብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል፡፡