null Poor follow up and week management was the major problem of the Hawasa-Bule Hora road project.

ከሀገሪቱ የልማት ኮሪደሮች አንዱ የሆነው የሀዋሳ-ቡሌ ሆራ መንገድ ፕሮጅክት  በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ዋናው ችግር የክትትልና ቁጥጥር ማነስ እንደሆነ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ፣

ቋሚ ኮሚቴው በደቡብ ክልል ከሀዋሳ-ቡሌሆራ እየተገነባ ያለውን 200 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸምን በአካል ተንቀሳቅሶ ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ ሪጅን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ጉቱ ፕሮጀክቱን አስመልክተው ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ባደሩጉበት ወቅት ግንባታው ከሚጠበቀው በላይ መጓተቱንና ለዚህም የኮንትራክተሮች መቀያየርና የጸጥታ ችግር መኖሩ እንደ ዋና ተግዳሮት ናቸው ሲሉ አንስተዋል፡፡

ይህ መንገድ ኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጅዎችን ለማካሳት፣ ኢንዱስቴሪውንና ንግዱን ለመደገፍ እንዲሁም ከኬንያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ታስቦ እየተሰራ ቢሆንም በአሁኑ ስዓት ባለው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሂደት የታሰበውን  እቅድ ማሳካት ስለማይቻል መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይገባል ብለዋል አቶ ደጀኔ፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ 200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እና ለሶስት የውጭ ኮንትራክተሮች ተከፋፍሎ የተሰጠ ሲሆን ከሀዋሳ-ጩኮ እና ከጩኮ- ይረጋጨፌ ያለው 126 ኪሎ ሜትር መንገድ በሶስት አመት ተኩል ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም በኮንትራክተር የአቅም ውስንነት ምክንያት ሊሳካ ባለመቻሉ ውሉ ተቋርጦ ለሌላ ኮንትራክተር በመሰጠቱ በአሁኑ ስዓት የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳለና በተለይ ከሀዋሳ-ጩኮ ያለው መንገድ ከ80 በመቶ በላይ መከናወኑን አክለው አስረድተዋል፡፡

ከይርጋጨፌ-ቡሌሆራ ያለው 74 ኪሎ ሜትር ፕሮጀት በተመሳሳይ በውጭ ኮንትራክተር የሚገነባ ቢሆንም በተመሳሳይ ከ6 አመት በላይ የፈጀና አሁንም ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተለይም የአመራሩን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ሲሉ በምእራብ ጉጅ ዞን በተካየሄደ የባለድሻ አካላት ውይይት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ፡፡

ለፕሮክቱ መጓተት የወሰን ማስከበር፣ የዲዛይን ለውጥና የጸጥታ ችግሮች በምክንያትነት የተገለጹ ሲሆን በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙት የወረዳ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው መንገዱ ለረጅም ጊዜ የተጓተተ ቢሆንም ሳይደናቀፍ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለው በኮንትራክተሩ በኩል ለአካባቢው ወጣት የስራ እድል በመፈጠር፣ ተለዋጭ መንገድ በመስራትና በመንገድ ስራው የሚፈጠረውን አቧራ ውሃ በማርከፍከፍ በኩል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

 

አክለውም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በወሰን ማስከበር ሳቢያ ንብረታቸው የተነካባቸው ግለሰቦችን የካሳ ክፍያ በማፋጠን መንገዱ ተጠናቅቆ ለታለመለት ዓላማ እዲውል ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ተቋራጮቹ በበኩላቸው የታዩትን ክፍተቶች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ለማረምና ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያሳየውን የባለቤትነት ስሜት በጥንካሬ አንስቶ የወሰን ማስከበር ስራው በተለይም የመብራትና የውሃ ተቋማት አፈጻጸም መዘግየት ለፕሮጀክቱ መጓተት በምክንያትነት የሚወሰድ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የካሳ ክፍያውን ማፋጠን እንዳለበትና ግለሰቦቹ ተገቢውን ግምት አግኝተው በፕሮጀክቱ ላይ ያላቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲጠነክር ማድረግ እንደሚገባው ያስገነዘበው ቋሚ ኮሚቴው ፕሮጀክቱ ከሀገሪቱ የልማት ኮሪደሮች አንዱ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ፕሮጀክቱ እጅግ የዘገየ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ መንግስት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳገኙ ያደረገ በመሆኑ በቀጣይ ሂደቱን ለማፋጠን እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡