null Project performance of Road in Guraghe Zone is low. Hence, it needs attention.

በጉራጌ ዞን የአጣጥ ማዞሪያ-ጉንችሬ-ቆሴ-ጌጃ-ሌራ መንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሻንዶንግ ሃይዌይ ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን በተባለ የቻይና ተቋራጭ ድርጅት የሚገነባውን 81 ኪ.ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸምን በአካል ተንቀሳቅሶ ተመልክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አቶ ተፈሪ ዘለቀ ፕሮጀክቱን አስመልክተው ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ባደሩጉበት ወቅት ግንባታው ጥቅምት 2010 ዓ.ም. መጀመሩንና በ42 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የተመደበውም በጀት ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንገዱ ደረጃ አስፓልት ኮንክሪት መሆኑን የገለጹት አቶ ተፈሪ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ከማስኬድ አኳያ የካሳ ክፍያ ግምት መጋነንና ግምት የተሰራላቸው የመብራት ኃይል ፖሎች በወቅቱ አለመነሳት ተግዳሮት ሆነዋል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙት የኢነሞርና ኢነር ወረዳ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው መንገዱ ለረጅም ጊዜ ስንናፍቀው የነበረ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳይደናቀፍ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለው በኮንትራክተሩ በኩል ለአካባቢው ወጣት የስራ እድል በመፈጠር፣ ተለዋጭ መንገድ በመስራትና በመንገድ ስራው የሚፈጠረውን አቧራ ውሃ በማርከፍከፍ በኩል ውስንነቶች ስላሉበት ሊያስተካክል ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በወሰን ማስከበር ሳቢያ ንብረታቸው የተነካባቸው ግለሰቦችን የካሳ ክፍያ በማፋጠን በኩል ችግር ስላለበት መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ኮንትራክተሩ በበኩሉ የስራ እድል ፈጠራው ላይ አብዛኛው ስራ ልምድ የሚፈልግ  መሆኑንና ልምድ በማይፈልጉ የስራ ዘርፎች ላይ የአካባቢውን ወጣቶች የቀጠረ መሆኑን አንስቶ የታዩትን ክፍተቶች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለማረምና ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያሳየውን የባለቤትነት ስሜት በጥንካሬ አንስቶ የወሰን ማስከበር ስራው በተለይም የመብራትና የውሃ ተቋማት አፈጻጸም መዘግየት ለፕሮጀክቱ መጓተት በምክንያትነት የሚወሰድ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብሏል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብ ግምት ሳይከፈለው ንብረቱን ማንሳቱ ለፕሮጀክቱ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የካሳ ክፍያውን ማፋጠን እንዳለበትና ግለሰቦቹ ተገቢውን ግምት አግኝተው በፕሮጀክቱ ላይ ያላቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲጠነክር ማድረግ እንደሚገባው ያስገነዘበው ቋሚ ኮሚቴው የተፈጠረውም የስራ እድል ዝቅተኛ በመሆኑ እየተስተካከለ መሄድ እንዳለበትና ለመንገዱ ጥራትም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ኮንትራክተሩ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከተሰጠው የ42 ወራት ጊዜ ውስጥ ከ15 ወራት በላይ ቢያስቆጥርም የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከ8 በመቶ በታች መሆኑ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን የሚፈታተን በመሆኑ ያሉትን ችግሮች እየፈቱ ለመሄድና የፕሮጀክቱን ሂደት ለማፋጠን እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡