null Projects started to modernize the agricultural the sector should finalized on scheduled.

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን 2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ግብርናውን ለማዘመን በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጓተት የሚታይባቸው መሆኑን አመላክቶ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ወደ ስራ ሊገቡ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይም በግብርና ትራንስፎርሜሽን የሚሰጠውን ድጋፍ አስመልክቶ በእርሻ አገልግሎት ተቋማት ለአርሶ አደሩ በሚያስፈልጉ በአግሮ ኬሚካል፣ በእንስሳት መድሃኒት እና በሌሎችም የግብዓት አቅርቦት ሽፋን ላይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባለፈ ተደራሽነታቸው ውስንነት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴ ጠቁሞ በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

የምጥን ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎችም መጓተት የሚታይባቸው መሆኑንና ግብርናውን ለማሸጋገር ክልሎች በግብርና መካናይዜሽን እንዲመሩ ኤጀንሲው ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ የማይቀጥል ከሆነ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ብሏል፡፡

በፕሮጀክቶች ፍትሃዊነትና ተደራሽነት፣ በባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች የተገኙ ስኬቶችን፣ በቆላማ ቦታዎች ስንዴን በመስኖ ማምረትን አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ ቦምባ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የፕሮጀክቶችን ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን በተመለከተ እራሱን የቻለ ዝርዝር መስፈርቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ለፕሮጀክቶች መጓተትም ትልቁ እንቅፋት የግዥ ስርዓቱ እና የግንባታዎች የዲዛይን ችግር መሆኑን በምክንያትነት አንስተው የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ አሁን ላይ ቅንጅታዊ ስራ መጠናከሩን አስረድተዋል፡፡

የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን አፈጻጸም በተመለከተም በሪፖርቱ ባለመካተቱ እንጂ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ አብራርተዋል፡፡

በቆላማ ቦታዎች ስንዴን በመስኖ ማምረትን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ አቶ ካሊድ ምላሽ በሰጡበት ወቅት በሶማሌ ክልል አዋሽ ተፋሰስ በ300 ሄክታር ላይ በመስኖ ስንዴ ለማምረት ታቅዶ 60 ሄክታር ላይ ብቻ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው በሌላ በኩል በሦስት ዓመት ውስጥ 10 ሄክታር ለማልማት ቢታቀድም እቅዱ በመሳካቱ ላይ ግን ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በስጋትነት ካነሷቸው መካከልም የመሬትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንደሆኑም ነው የገለጹት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኤጀንሲው ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት አንጻር ክፍተቶች እንዳሉበት ከመስኖ ልማቱ እቅዱ መረዳት እንደሚቻል አመላክተዋል። የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለአርሶ አደሩ የግብርና የዘር ብዜትና ምርምር እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ / አልማዝ መሰለ በበኩላቸው የመስኖ ፕሮጀክትና የአፈር ለምነት ጥናቶች መደረጋቸውን፣ በዘርፉ ኢንቨስት የሚደረገውን ወጪ ለማወቅ ጥረት መደረጉን እና አዲስ የመካናይዜሽን ፕሮጀክት ለማቋቋም የሚደረገውን ሁለንተናዊ ርብርብ በጠንካራ አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡

በሌላ በኩል የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ውጤታማ አለመሆናቸውን እና የምጥን ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በተመለከተ ፖታሹ ከአርሶ አደሮች መጋዘን አለመወገዱን በክፍተት አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የቅንጅታዊ አሰራር ማነቆዎችን ለመቅረፍ እርብርብ መደረግ እንዳለበት እና ፕሮጀክቶች ለሌላ ወገን በሚተላለፉበት ወቅት የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ / አልማዝ መሰለ አሳስበዋል፡፡