null Projects working in the country by loan and aid should be fair.

በሀገሪቱ በብድርና ዕርዳታ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ፍትሀዊ፣ ተደራሽና ተግባራዊ ስለመደረጋቸው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኃላፊነት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡ 

ይህ የተገለፀው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑንና ተጠሪ ተቋማት የሆኑትን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትንና የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲን የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርትን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ወቅት የተገኙ ውጤቶችና የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችን፣ በእቅድ ተይዘው ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ክንውኖችን፣ የዘላቂ ልማት ፍላጎት መተግበሪያ ዳሰሳ ጥናት ለማዘጋጀት ቢታቀድም አለመሰራቱን እና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው 4ኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መዘግየቱን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በዋነኛነት አንስቷል፡፡

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ወቅት የተገኙ ውጤቶችና የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችን በሚመለከት እቅዱ ሲዘጋጅ ታሳቢ የነበሩ በርካታ ግቦች ቢኖሩም በሀገሪቱ ባለፉት 3 አመታት በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ሊሳኩ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። በማኑፋክቸሪንግ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በወጪ ምርቶች፣ በማዕድን፣ በመንገድ ስራ ላይ ማነቆዎች እንደነብሩ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ከሚመለከታችው 6 መ/ቤቶች ጋር በመነጋገር ማሻሻያና የግብ ክለሳ መደርጉን ምላሽ ሰጥተዋል። በቀሩት ወራትም የማካካሻ ስራዎች እንደሚሰሩም አብራርተዋል። የዘላቂ ልማት ግቦች ፍላጎት መተግበሪያ ዳሰሳ ጥናትን በሚመለከት ጥናቱ የዘገየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን መጠናቀቁን ነው የገለፁት።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በበኩላቸው ኤጀንሲው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 4ኛውን አገራዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለማካሄድ ሲዘጋጅ ቆይቶ በ2010 ቆጠራውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ቢያጠናቅቅም በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ወደ 2011 ዓ.ም መሽጋገሩንና ቆጠራውን በመጋቢት ወር መጨረሻ ለመጀመር በቆጠራው ላይ ሚሰማሩ 190,000 ሰራተኞች ምልመላና ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ምላሽ ሰጥተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በእቅዱ ውስጥ ለተቀመጡ ግቦች አለመሳካት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው ሁኔታን በምክንያትነት ማንሳቱ ተቀባይነት እንደሌለውና ችግሩ ባልተፈጠረባችው አካባቢዎችም ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደሆነ፣ እቅዱም በጥቅል የቀረበ እንጂ የተከናወኑና ያልተከናወኑ ተግባራትንም በአግባቡ ለይቶ እንደማያሳይ ጠቁመዋል።  

ኮሚሽኑም በብድርና በእርዳታ ገንዘብ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ፍትሀዊ ተደራሽነታቸውን እና ተግባራዊ መደረጋቸውን የማረጋገጥ ሀላፊነት እንዳለበት አመላክተው፤ በቀጣይ የማካካሻ ስራዎችን በመስራት ዝቅተኛ አፈጻፀም ያላቸውን ግቦች ማሳካት እንደሚገባም አሳስበዋል።        

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ለምለም ሀድጎ ኮሚቴው ያዘጀውን ግብረ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽኑ የ2010 በጀት አመት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻፀም ሪፖርት አዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት ሙሉ በሙሉ ማሰራጨት መቻሉን፣ 6 የመንግስት ፕሮጀክቶች መመሪያዎች ስራ መጠናቀቁን፣ ብሄራዊ ኢኮኖሚ አካውንት መረጃ በእቅዱ መሰረት ተዘጋጅቶ ለሚመለከታችው አካላት መዳረሱን በጠንካራ አፈጻፀም አንስተዋል።

በሌላ በኩል ከእቅድ በታችና ዝቅተኛ አፈጻጸሞች መኖራችው፣ የመደበኛና ካፒታል በጀት በፕሮግራሞች በዝርዝር ተለይተው አለመቅረባቸውን በእጥረት አስቀምጠዋል።

በመጨረሻም የም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አዲስ አደረጃጀትን ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈጻሚ ተቋማት ላይ ለሚያደርጉት የክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ተግባር አፈጻፀም መመዝኛ መስፈርቶች መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ለኮሚሽነሩ በተዘጋጀው መመዘኛ መስፈርቶች ላይም ውይይት ተደርጓል።