null Elections and Political Parties draft law enable the Competing political parties to cooperate with the winning party.

 የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ-ህግ  ተፎካካሪ  የፖለቲካ  ፓርቲዎች  ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር ተደጋግፈው ለመስራት የሚያስችል እንደሆነ ተገለጸ ፡፡

ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ- ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማህበራት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ምርጫውን ተዓማኒ ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ አሰራርን የተከተለ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡

በውይይቱም በረቂቅ -ህጉ መሻሻልና መካተት አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ዙሪያ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ ማህበራ ተወካዮች መክረዋል፡፡

በተሳታፊዎቹ በኩል ከተነሱት ማሻሻያዎች በተጨማሪ በረቂቅ-ህጉ ሊካተቱ ይገባቸዋል የተባሉ አስተያየቶች ካሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው በጽሁፍ ማቅረብ እንደሚሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺዕመቤት ነጋሽ አሳውቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅማቸውም እንደማይከር በሚዘረዝረው  ረቂቅ-ህግ አንቀጽ 33 ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል ፡፡

በደመወዙ ኑሮውን መደጎም ያልቻለን የመንግስት ሰራተኛ ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ደመወዙና ጥቅማ-ጥቅሙ አይከበርም ማለት ወደ ምርጫ አትግቡ ከማለት ለይተን አናየውም ብለዋል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ፡፡

የመንግስት ሰራተኞች  በስራ ሃላፊነት ያገኙትን ስልጣን ፣ የመንግስትንና የህዝብን  ሃብትና ንብረት ለምርጫው አገልግሎት እንዳያውሉት  ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ   ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ ህጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች  ምስረታ ጀምሮ  እስከ የመስራች ቁጥር አባላት ድረስ አዳዲስ አሰራሮችን  እንዳካተተም  ተገልጿል፡፡

አንድ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ በረቂቅ ህጉ  ተጠቅሷል፡፡

ሃገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የተጠቀሰውን የመስራች ቁጥር አባላት  ለማሟላት እንደሚቸገሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል፡፡

መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሃገር  የተጠቀሰውን የመስራች ቁጥር አባል ማሟላት አስቸጋሪ እንደማይሆን ወይዘሪት ብርቱካን  አብራርተዋል፡፡

 በግንቦት ወር 107 የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አሁን ላይ 137 እንደደረሰ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል፡፡