null Speaker of the House of People's Representatives, Ato Tagesse Chafo, said, "If we have learned from past mistakes and forgiven our mistakes we should build on our future values.

ወቅቱ ካለፉ ስህተቶቻችን ተምረን ይቅር በመመባባል ወደፊት የሚያሻግረንን ተግባር የምነከናውንበትና የአብሮነት እሴቶቻችንን የምንገነባበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ፣

የውይይቱ መነሻ ሃሳብ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የጠፋውን የሰው ህይወትና ንብረት እንዲያጣራ የተመረጠው አጣሪ ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት ሲሆን ከ13 አመታት የስደት ኑሮ በኋላ ወደ አገራቸው የገቡት የወቅቱ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል ሪፖርቱን አቅርበዋል፡፡

በወቅቱ ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ ተከትሎ በተከሰተው ሁከት የጠፋውን የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት አጣርቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርብ 11 አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚሽን በአዋጅ መቋቋሙን የገለጹት አቶ ፍሬህይወት ነገር ግን በተደረገው የማጣራት ሂደት በርካታ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙንና ከ50 ሽህ በላይ ዜጎች መታሰራቸውን እንዲሁም የጸጥታ ኃይሉ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ መውሰዱን የሚያረጋግጥ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበናል ብለዋል፡፡

በወቅቱ የነበሩት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የቀረበውን ሪፖርት በግብዓትነት ወስዶ የማስተካከያ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሪፖርቱን በማስተባበል እንዲስተካከል በኮሚሽኑ አባላት ላይ ጫና በመፍጠራቸው ምክንያት ሁከትና ብጥብጡ እየባሰ ሄዶ በህዝብና በመንግስት መካከል አለመተማመን ነግሶ መቆየቱን አቶ ፍሬህይወት አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ትክክለኛና ሚዛናዊ ቢሆንም በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው ባለስልጣናት ተቀባይነት ባለማግኘቱ በኮሚሽኑ አባላት ላይ ለህይወት የሚያሰጋ ዛቻና ማስፈራራት ስለደረሰብን የኮሚሽኑ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ለስደት ተዳርገን ቆይተናል ብለዋል፡፡

ይህም ሆኖ አሉ የቀድሞው የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና የምርጫ 1997 ዓ.ም. ሁከትና ብጥብጥ አጣሪ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ ፍሬህይወት ዮሐንስ የበቀል ስሜት እንደሌላቸውና እስካሁን ከተፈጠረው ስህተት ተምረን ይቅር በመመባባል ወደፊት የሚያሻግረንን ተግባር ማከናወን ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በወቅቱ ለተፈጠረው ሁከት ዋናው ምክንያት የምርጫ ውጤት ሳይገለጽ ከአንድ ወር በላይ መዘግየቱ እንደሆነ የገለጹት አቶ ፍሬህይወት ይህም ህዝቡን ለጥርጣሬ እንደዳረገውና በቀጣይም የምርጫ ውጤት ፍጹም ተአማኒ በሆነ መንገድ በወቅቱ መገለጽ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት አደረጃጀት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ፍሬህይወት ከዚህ በኋላ ትንንሽ ቁስሎችን በመነካካት ነገሮችን ከማባባስ ይልቅ ህዝብን ወደ ይቅርታና ወደ አንድነት በሚያመጡ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የቀረበውን የውይይት መነሻ ሃሳብ አድንቀው ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ በህዝብና በመንግስት መካከል የተፈጠረው ክፍተትና አለመግባባት እንዲሁም የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊ እንደነበር ገልጸው ከዚህ በኋላ መቆም እንዳለበትና የአብሮነት እሴቶቻችንን መገንባት ላይ ማተኮር  እንዳለብን አስገንዝበዋል፡፡

አፈ-ጉባኤው አክለውም የተቋማት አደረጃጀቶችን በማስተካከል ህግና ስርዓትን ተከትለው እንዲሰሩ ማድረግና አገራችን ከገባችበት ችግር ወጥታ የህዝቦች አንድነትና ልማት የተረጋገጠባት እንድትሆን ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡