null Speaker requests citizens cautious against #COVID-19

አፈ-ጉባዔው የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛመት የጥንቃቄ ማሳሰቢያ ሰጡ

መጋቢት 18፣ 2012፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክቡር ታገሰ ጫፎ፤ ኮቪድ-19 በሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ የሚታወቀው ቫይረስ በሀገራችን እንዳይዛመት መላው የሀገራችን ሕዝቦች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስገነዝብ ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡

ክቡር አፈ-ጉባዔው በዛሬው ዕለት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት በዚሁ ማሳሰቢያ፤ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ቫይረሱ እያስከተለ ካለው ቀውስ አንጻር የጥንቃቄ ርምጃዎችን መተግበር ለነገ የማይባል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሀገራችን የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክር ተቀብሎ መተግበር ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅትም የቫይረሱን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የስርጭት አድማስ እንዲሁም መደረግ አለባቸው ብሎ የሚያወጣቸውን ሙያዊ መመሪያዎች ሳናቅማማ መፈፀም እንደሚገባም አቶ ታገሰ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር መንግስት የቫይረሱን ሀገራዊ ሁኔታ በተመለከተ በቅርበት እየተከታተለ ለሁሉም ዜጎች የሚያስተላልፋቸው ምክሮችም የማይዘለሉ መሆናቸውን ያወሱት ክቡር አፈ-ጉባዔው፤ የመንግስት ውሳኔዎችም ሊተገበሩ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ አያይዘውም፤ ዜጎች ዓቅማቸው በፈቀደ መጠን የመንግስትን ጥሪ በመቀበል በሀብት አሰባሰቡም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

አቶ ታገሰ በተጨማሪም፤ በአንጻራዊነት የጥንቃቄ ተግባራት እየተተገበሩ ቢሆንም፣ የጥንቃቄ ጉድለቱ ገና በሚፈለገው ደረጃ አለመደፈኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቸልተኝነትን ማስወገድ እና ጥንቃቄ፣ ጥንቃቄ እንደዚሁም ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ማንኛውም ሰው የራሱን ድርሻ ከመወጣት ባሻገር፤ ምክር መቀበል፣ መታዘዝ እና መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ያለፈውን ለፈጣሪ እንተዋለን፡፡ ይህንን አድርገን፣ ሁላችንም አብረን በመቆም የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ለማስቻል የድርሻችንን እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል ክቡር አፈ-ጉባዔው፡፡

እንደተለመደው ሁሉ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲባርክ የተመኙት አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎችን እና ሌሎች ሥራዎችን ሰርዞ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተሰጡት ሀገራዊ አቅጣጫዎች ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

 

በ አሥራት አዲሱ

  የምክር ቤት ፀሐፊ