null Standing committee of the House Convinced Howassa Water project to work with stakeholders to solve electricity problems.

የሐዋሳ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ያጋጠመውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይገባዋል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ መስኖና ኢነርጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው የሐዋሳ ከተማ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አፈጻጸምን ሰሞኑን በአካል ተንቀሳቅሶ ተመልክቷል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ውሃና ሳኒቴሽን ድርጅት ዋና ስራ-አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሌላሞ እንዳሉት  ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ስራ ቢጀምርም ከመብራት መቆራረጥ ጋር ያለው ችግር ባለመፈታቱ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት መስጠት አልቻለም ብለዋል፡፡

አያይዘውም ከከተማው መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የማስፋፊያ ስራ ማስፈለጉንና የሚወገደውን ፍሳሽ መልሶ በማከም ለአገልግሎት እንዲውል ማስቻል የፕሮጀክቱ አላማ መሆኑን አስረድተው ይህንንም ለማሳካት የሚያስችል ከ5-20 አመት የሚደርስ ፕሮጀክት ተነድፎ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እንደ አገር የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ሲሆን የፍሳሽ አወጋገድና አጠቃቀም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ያሉት ስራ-አስኪያጁ በ2012 በጀት አመት ወደ ተግባር መግባት የሚያስችለንን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡

ከተሞች ቱሪስት የሚመጣባቸው ብቻ ሳይሆኑ ገብቶ የሚቆይባቸው እንዲሆኑ ለፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ፕሮግራም ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የጠቆሙት ስራ-አስኪያጁ ከተሞችን ማራኪና ተወዳዳሪ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራትና የፕሮጀክቱን ጽዱ ከተማ የመፍጠር አላማ በተያዘለት 6አመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትና መሰረተ-ልማቶችም እርስ በእርሳቸው እንዳይጠፋፉ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁሞ ፕሮጀክቱ ሲሰራ ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ከወዲሁ አስቦ መስራት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በስምሪቱ የሐዋሳ ሜትሮሎጅ ድርጅትን የስራ እንቅስቃሴም ተመልክቷል፡፡

በምከታውም ወቅት በሰጠው አስተያየት ተቋሙ ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱና በተለይ የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ መሳሪያ መገንባቱ በአካባቢው ያለውን ብክለት ለመቆጣጠርና ተቋማት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ የሚረዳ በመሆኑ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጅ ሊጠናከር ይገባል ብሏል፡፡