null The 2019 budget should focus on activities that will ensure the benefit of the people and the interests of citizens.

የሚመደበው የ2012 በጀት ፍትሐዊና የዜጎችን ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ተባለ፡፡

ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓ.ም 43ተኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል የመንግስት የ2012 ረቂቅ በጀት በተመለከተ በቀረበው የበጀት መግለጫ ላይ በመወያየት ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀጥታ መርቷል፡፡

የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ መግለጫውን ያቀረቡ ሲሆን የዘንድሮ በጀት በባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ያጋጠመውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመሻገር አዲስ መሰረት በተጣለበትና በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም በዛው ልክ በርካታ ተግዳሮቶች የተስተናገዱበት እንዲሁም በኢኮኖሚው ረገድ በቀድሞው መጠን ማደግ ያልቻለ በመሆኑና አለም አቀፋዊ፣ አገር ውስጥ ነባራዊ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባትና ለቀጣይም ሊመጣ የሚችለውን ከግምት በማስገባት ለ2012 ባጠቃላይ የፌዴራል መንግስት የወጪ በጀት 387 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ነው በመግለጫው ላይ ያስቀመጡት፡፡

ለ2012 የተበጀተው ከ2011 ከጸደቀው ጋር ሲነጻጸር በ6.1 ቢሊዮን ወይም 1.6 በመቶ ጭማሪ እንዳለውና አጠቃላይ ከተያዘው ለመደበኛ ወጪ 109.5 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ብር 130.7 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግስት ድጋፍ ብር 140.8 በቢሊዮን እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 6 ቢሊዮን ተደግፎ የቀረበ ከመሆኑም በተጨማሪም በዋናነት ድህነትን ለማስወገድ እና ማክሮ ኢኮኖሚውን በመደገፍ እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለዘላቂ ልማት ግቦች ድጋፍና የዜጎችን የሃብት ልዩነት ለማጥበብም ታስቦም እንደሆነም ነው፡፡

ም/ቤቱም በቀረበው መግለጫ ላይ አስተያየት የሰጠ ሲሆን አሁን ላይ በጣም አሳሳቢ እየሆነ ያለውን የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ በተለይ በመግለጫው እንደተቀመጠው ምግብ ነክ በአሃዝ 11.5 ከመቶ ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆነው ደግሞ 13.8 ከመቶ መድረሱ አብዛኛውን ማህበረሰብ ከፍተኛ ችግር እና ምክኒያቱም የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ማነስ፣ በተለያዩ አከባቢዎች አለመረጋጋትና የምርት አቅርቦት ማነስ ታሳቢ መደረግ እንዳለበትና ለቀጣይ ለመቆጣጠር የፋይናንስ አሰራርን በመዘርጋት መሰራ አለበትም ብሏል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ የታክስ ገቢ ለማሳደግ በመወሰን ላይ ያለው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ እንቅስቃሴ እንደሆነ ቢገለጽም ባለፈው ዓመት የታክስ ገቢ በታቀደው አለመከናወኑ የአገሪቱን እድገት የኋሊት ሲጎትታት የቆየና በ2012 በጀት ላይ እንቅፋት እንዳይሆን መስራት እንዳለበትና ምክር ቤቱ ይህንን ክፍተት ለማሟላትና በጀትን ለመደገፍ 34 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ከዓለም ባንክ መገኘቱ መልካም ቢሆንም አሁንም የውስጥ አቅምን ማሳደግ ከምንም በላይ ወሳኝ እንደሆነ አንስቷል፡፡

ም/ቤቱ በበኩሉ ሚኒስትሩም በመግለጫው የ2012 በጀት የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ፖሊሲ ትንበያዎችን እና ዝርዝር ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መቅረቡን ደግፈው አሁንም በተቋማት ላይ የሚታየው የበጀት ብክነት እና የፕሮጀክቶች ትግበራ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን መልሶ የአገሪቱን በጀት የሚጎዳ ስልሆነም ትኩረት መሰጠት እንዳበት ነው፡፡

የፌዴራል መንግስት ለክልሎች መሰረተ ልማት ማስፈጸሚያ የሚሰጠው የድጎማ በጀት ከዚህ በፊት በም/ቤቱ ከፍተኛ የፍትሐዊነት ጥያቄ ሲያስነሳ የቆየ እንደሆነ ቢነሳም አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ከአስፈጻሚ አካላትና ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን የሚነሱ ከፍተኛ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችልና በጂዲፒ ተይዘው ሳይሰሩ ሲንከባለሉ የቆዩትን ለመስራት የሚያስችል በጀት እንደተያዘ ለቀጣይ ከፌዴሬሽን ም/ቤት ጋር ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ሚኒስትር አህመድ ሺዴ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ሚኒስትሩ በልማት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ በምንገነባው የጋራ አገራችንን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ድህነትን በማስወገድ በአንጻሩ ዕድገትን በማስመዝገብ ሁላችንም በያለንበት መረባረብ እንዳለብን ያሳሰቡ ሲሆን ም/ቤቱም የቀረበውን ረቂቅ የበጀት አዋጅን አዋጅ ቁጥር 63/2011 ሆኖ በቀጥታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በቀጥታ መርቷል፡፡