null The activities to benefit women and youth in the Somali Regional State in Citi and Fafan zones need to be further strengthened.

በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሲቲ እና በፋፋን ዞኖች ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት አመርቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ግንቦት 12 ቀን 2011 .. የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች /ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ በሲቲና ፋፋን ዞኖችና በስራቸው በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በወጣቶችና ስፖርት፣ በሴቶችና ህጻናት እንዲሁም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ባደረገው የመስክ ምልከታ ቃኝቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው በጅግጅጋ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን፣ የተሻለ የወጣት ማዕከል መኖሩን፣ ወጣቶችን በማደራጀት የስራ እድል መፈጠሩን እንዲሁም የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ሥልጠና መሰጠቱን፣ በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጀቶች ጋር በመሆን ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና መሰጠቱንና 1,525 ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን፣ በፋፋን ዞን ቀብሪበያ ወረዳ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን በጥሩ አፈጻፀም ተመልክቷል፡፡

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመከላከል አኳያ በክልሉ የሚታይ ችግር ባይኖርም ከመሀል ሀገር ከልሉን አቋርጠው ወደ ጀቡቲና ሶማሊ (ቦሳሶ) የሚሄዱ ህገ-ወጥ ወጣቶችን በራስ ወጪ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ወደቀያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረትንም ቋሚ ኮሚቴው አድንቋል፡፡

በሌላ በኩል የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በአግባቡ ያለመደራጀቱን፣ የወጣቶች ስብእና መገንቢያ ማዕከል ተግባራዊ አለመሆኑን፣ የስፖርት ትጥቅና መሳሪዎች አለመሟላታቸውን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ አዋጅ ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩን፣ በህልና ሀይማኖት ተፅእኖ ምክንያት በስፖርቱ ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆንን፣ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ግብረ ሀይል በአግባቡ አለመደራጀቱን፣ የጅግጅጋ ስታዲም ግንባታ ጥሩ ቢሆንም ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውንና በይዞታው ክልል ውስጥ የግለሰቦች መኖሪያ ቤት መሰራቱን ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው አረጋግጧል፡፡

በተመሳሳይም በቀብሪበያ ወረዳ ወጣቶች መደራጀታቸው ቢገለጽም ወደስራ የገቡ አለመኖራቸውን፣ በቂ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች አለመኖራቸውን፣ የአካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት የማገገሚያ ማዕከል ግንባታ ቢጀመርም ተጠናቆ ወደስራ አለመግባቱን እንዲሁም ሴቶችን በማህበራት በማደራጀት ወደስራ እንዲገቡ ቢደረግም የተጠናከረ አለመሆኑን ነው ቋሚ ኮሚቴው የተመለከተው፡፡

በቀጣይም የሴቶችንና ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በስራ ዕድል ፈጠራና ስብዕና ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰራ ኢንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡