null “Agreements with Eritrea has to be dealt with on the basis of institutional frame works”. Said the standing committee.

 ከኤርትራ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  በትኩረት መስራት እንደሚገባው የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱን  የ መቶ ቀናት እቅድና የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

የሃገራችን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከጎረቤት ሃገሮች ጋር  መልካም ጉርብትናንና ቀጠናዊ ሰላምን ማጠናከር ላይ በስፋት እየተሰራበት እንደሆነ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ  አብራርተዋል፡፡

የጎረቤት ሃገሮች ግንኙነት በሰላምና በምጣኔ ሃብት ረገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃገራችን ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ስላለው በቀጠናው የተፈጠረውን  ሰላም አጠናክረን እንቀጥላለን  ሲሉ ዶ/ር ወርቅነህ  ለቋሚ ኮሚቴው  ተናግረዋል፡፡ 

ከጎረቤት ሃገር ኤርትራ ጋር  ለበርካታ አመታት የነበረው አለመግባባት ተፈቶ ህብረተሰቡ ያለምንም ችግር  የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች  እያደረገ እንደሚገኝ  ጠቅሰዋል፡፡

  ከኤርትራ ጋር  የተፈጠረውን መልካም  ጉርብትናና ትስስር  አጠናክሮ ለማስቀጠል  የኢምግሬሽን፣ የንግድ፣ የታክስ፣  የከርንሲ/ የምንዛሬ/ ፣ የጉምሩከና  የድንበር ጉዳዮች ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉ ያላሰለሰ  ሶስት ዙር  ተከታታይ  የሆኑ ውጤታማ ድርድሮቸ  እንደተካሄዱ  ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ከሶማሊያ  ጋር በተያያዘም በሃገሪቱ የመጣው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፌደራል መንግስቱ ጋር  የተጠናከረ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤  ለሃገሪቱ አለም አቀፍ እርዳታዎች  ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ  በኢትዮጵያ በኩል የዲፕሎማሲ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ዶ/ር ወርቅነህ  ተናግረዋ፡፡

 ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደረጉ  የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን   በተመለከተ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የደቡብ ሱዳን ነጻነት ትግል ጀምሮ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግ የነበረች ሃገር መሆኗን አውስተው፤  በሃገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታ    ከብዙ ውጣ ውረድና እልህ አስጨራሽ ድረድሮች  በኋላ በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ አንጻራዊ ሰላም  እንደሰፈነ ገልጸዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ፣ ጅቡቲ ና ሱዳን ኤርትራን ለማቀራረብ ና የቀጠናውን ሰላም ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማምጣት ኢትዮጵያ አኩሪ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሰራች ዶ/ር ወርቅነህ  አብራርተዋል፡፡

የውጭ ሃገር  ዜጎቻችን በተመለከተም  በዋናነት በመካከለኛው ምስራቅና በምዕራቡ አለም የሚኖሩ ዜጎቻቻን  ከኤምባሲ  እስከ ሃገራቸው  መንግሰት  ድረስ  የነበረው የፖለቲካ አለመግባባት እንደተቀረፈ ሚኒስትሩ  አብራርተዋል፡፡  

የውጭ ዜጎቻችን መብት ለማስከበር፣ የታሰሩትን ለማስፈታት  እና  ለሚሰሩት ስራ  ተመጣጣኝ ገንዘብ እንዲከፈላቸው ለማድረግ   ከፍተኛ ስራ እንደተሰራም  ዶ/ሩ  አክለው ተናግረዋል፡፡

.በሃገራችን እየተደረገ ያለውን ለውጥ መሰረት በማድረግ የተለያዩ የአለም የፋይናንስ ተቋማት ለውጡን  እየደገፉት እንደሚገኙና አብረው እየሰሩ እንደሆነ  የገለጹት ዶ/ር ወርቅነህ፣ በዲፕሎማሲ ስራዎችም ተጨማሪ ወዳጅ ሃገሮች  ማፍራት እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡