null The Document Authentication and Registration Agency should give legal authentication documentations.

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ለትክክለኛ የሰነድ ባለቤቶች ማረጋገጫ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲን የወራት ዕቅድ አፈፃፀምን ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ገምግሟል፡፡

ኤጀንሲው አገልግሎቱን ፍትሐዊና ተደራሽ ለማድረግ  አሰራሩን ወደኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መለወጡና በብቁ ባለሙያዎችም አገልግሎቱ እንዲሰጥ የክሂሎት ክፍተት የሚሞሉ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠቱ በጥንካሬ ተገምግሟል፡፡

የተሟላ ሰራተኛ ኤጀንሲው ባለመያዙ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያስከተለው ቅሬታ እንዲፈታ እና ከአምናው አፈፃፀማቸው ዝቅ ያሉባቸው የአንዳንድ ተግባራት አፈፃፀም እንዲሻሻል ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦችና ተቋማት በሌላ ሰው ሀብትና ንብረት ዕውቅና ለማግኘት የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዳለ ኮሚቴው ጠቁሞ በሰነድ የማረጋገጥ ሂደት የሰነዱን ባለቤት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚሰራ ስራ ካለ እንዲብራራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ መረሳ ገብረ ዮሐንስ ሰራተኛው በስራ ጫና ውስጥ ባለጊዜ ደላሎች  በሌላ ሰው ሀብትና ንብረት ዕውቅና ለማግኘት የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚሞክሩ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ በኩል ያለው ችግር በመደበኛ የማጣራት ሂደት የሚፈታ መሆኑን በማመልከት ሌላ አሰራር አለመዘርጋቱን ነው የገለፁት፡፡

በሰራተኛው በኩል እንዲህ ዓይነት ጥፋት ተፈፅሞ ሲገኝ ሰራተኛው ታግዶ የተሰጠው ማረጋገጫ ወይም ምዝገባ እንደሚሻር ጠቅሰው በተጭበረበረ ሰነድ የተደረገ ምዝገባ ወይም ማረጋገጫ ሪፖርት ከቀረበበት ወዲያው የሚታረምበት አሰራር መኖሩን አመልክተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴውን ስብሰባ የመሩት የተከበሩ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ በለጠ የኤጀንሲው የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን አመልክተው በተለይም በሌላ ሰው ሀብትና ንብረት ዕውቅና ለማግኘት የሚደረጉ የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎት ሙከራዎች ሴቶች የንብረት ባለቤት የመሆንና ንብረት ማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ስለሚጋፋ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡