null The Enquiry Board attends report of Minister’s Committee

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቋቋመውን የሚንስትሮች ኮሚቴ የ1 ወር የስራ አፈጻፀም ሪፖርት አዳመጠ፤ በሪፖርቱ ላይም ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡

ግንቦት 06 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) ቦርዱ ዛሬ ባካሄደው የጋራ ስብሰባ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቋቋመውን የሚንስትሮች ኮሚቴ የ1 ወር የስራ አፈጻፀም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

የሚንስትሮች ኮሚቴን የ1 ወር የስራ አፈጻፀም ሪፖርት ያቀረቡት የኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር ም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኮሚቴው አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችል 5 ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም እና ዕቅድ በማዘጋጀት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

አዋጁ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መንገድ እንዲፈጸም ለማድረግ ክልሎችም ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት በመቀበልና ማስፈጸሚያ ደንቡን በመረዳት ስምሪት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ዝርዝር ተግባራትን ለመፈጸም የሚያስችሉ 5 መመሪዎችን ማዘጋጀቱን ጠቁመው፣ መመሪዎቹም የህግ ማዕቀፍ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የግብይይት፣ ሀይማኖት ተቋማት ሀይማኖታዊ ክንውናዊ እና የአሰሪና ሰራተኛ ስምሪት ስርዓቶችን ለመምራት የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኮሚቴው ወረርሽኙን በተመለከተ ግንዛቤ በማስጨበጥና ታች ድረስ መውረዱን በመከታተል፣ በአዋጁና ማስፈጸሚ ደንቡ የተቀመጡ ክልከላዎች ተግባራዊ ስለመደረጋቸውና በየደረጃው የሚገኘው አመራር ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነወይ? በሚሉት ጭብጦች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን በተከናወኑ ስራዎችም የሀይማኖት ተቋማት ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ ለረዥም ዘመናት ሲካሄዱ ነበሩ ሀይማኖታዊ ስርአቶች እንዳይካሄዱ በማድረግ፣ የዚህን የቁርጥ ቀን ጥሪ የተቀበሉ የጤና ባለሙዎች፣ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙዎች፣ ህግ አስከባሪዎች እና ሌሎችም በየደረጃው ያሉ አካላት ባከናወኗቸው ተግባራት ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይም ግንዛቤን በማሳደግ፣ የግብይይት ስርኣቱን በማስተካከል፣ የትራንስፖርት ችግሩን በመቅረፍ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡና በሚወጡ ዜጎች ላይ ቁጥጥር በማድገግና ከክሎችና ከሌሎች ኣጋዥ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበትም ቦርዱ በ1 ወር ውስጥ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትን አቅርበዋል፡፡

ቦርዱ በጤና ሚኒስቴር፣ በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአካል በመገኘት ወረርሽኑን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እና አዋጁን ተፈጻሚነት በተመለከተ በመስክ ምልከታው የተመለከታቸውን     ጠንካራና ደካማ አፈፃፀሞችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

በሁሉም ተቋማት የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና አዋጁን ለማስፈጸም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት፣ በትራንስፖርት ዙሪያ ማነቆዎች መኖራቸውን፣ አዋጁን ተላልፈው የተገኙ ዜጎችን በቶሎ ፍርድ እንዲገኙ ከማድረግ አንፃር አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች መሆናቸውንና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም የሁሉንም ወገን ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡

የቦርዱ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አዋጁን ለማስፈጸም የሚወሰዱ ህግን የማስከበር እርምጃዎች በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ በመግለጽ ላይ ያሉ አካላት በመኖራቸው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

ክቡር ም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት ምላሽ አዋጁ የወጣው የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እንጂ ለመጉዳት አለመሆኑን ጠቁመው፤ በአዋጁ የተቀመጡ ገደቦች በወረርሽኙ ሳቢያ የዜጎች ህይወጥ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መገንዘብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቦርዱ የሚንስትሮች ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት የሰጠው ግብረ መልስ ለቀጣይ ስራ አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡       

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት አገራዊ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በቀጣይም ቦርዱ በተሻለ መንገድ እንደሚሰራ እና በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ የሚፈቱበትን መንገድ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡                    

ዘጋቢ፡- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ