null The Ethiopian Bio-technology Institute should continue on the Economy and social problems to solve by research.

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት በአገራችን ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በምርምር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩትን የስራ እንቅስቃሴ በአካል ተመልክቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ የተቋማቸውን የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ገለጻ በአደረጉበት ወቅት እንዳሉት ተቋሙ እንደ አዲስ ከተደራጀ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በአገሪቱ ስር ሰድደው የቆዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ በርካታ የምርምር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባዮቴክኖሎጅ ህይወት ያላቸው አካላት ወይም በእነሱ የሚፈጠሩ ውጤቶችን ዘመናዊ የቤተ-ሙከራ ዘዴዎችን በመጠቀምና ሂደታቸውን በማሻሻል በግብርና፣ በህክምናና ኢንዱስትሪ መስኮች ተግባራዊ በማድረግ ለሰው ልጆች ጥቅምን የማረጋገጥ ሂደት ሲሆን በአገራችንም በተለይ የግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ አለመሆን እና ምርታማነቱን በሚፈታተኑ ማነቆዎች የተያዘ መሆኑ፣ በኋይል አቅርቦት ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችና በጤናው ዘርፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ትልቅ ፈተናዎች በመሆናቸው ተቋሙ እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ምርምር እያከናወነ መሆኑን ነው ዶ/ር ካሳሁን የተናገሩት፡፡

የኢንስቲትዩቱ የምርምር ስራዎች በአብዛኛው በግብአትነት የሚጠቀሙት የኢንዱስትሪ ተረፈ-ምርቶችን እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ቴክኖሎጅ ወጪ ቆጣቢና በቀላሉ የሚገኝ ከመሆኑም ባሻገር የአካባቢውን ንጽህናና ስነ-ምህዳር በማስተካካለ በኩል የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዶ/ር ካሳሁን አክለውም ተቋሙ የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ እንዲወጣና አገራችን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንዲሁም የብዝሃ-ሕይወት ሃብታችንን በዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂ በመጠቀም ለኢኮኖሚያዊ እድገት ለማዋል እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና የመንግስት እገዛ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ብለው ተቋሙ በምርምሩ ዘርፍ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማግኘት የተቸገረ በመሆኑ መንግስት የመዋቅር ማሻሻያ ጥያቄያችንን ሊቀበለንና ችግራችንን ሊፈታልን ይገባል ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በተቋሙ የተጀመሩት የምርምር ስራዎች የአገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ከመፍታት አኳያ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስቶ በተለይ አብዛኛዎቹ የምርምር ስራዎች በግብዓትነት የሚጠቀሙት የኢዱስትሪ ተረፈ-ምርትን መሆኑ ወጪ ቆጣቢ ብቻም ሳይሆን በረሃማነትን በመከላከል በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም የምርምር ስራዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ተለቅቀው የአገሪቱን እድገት ማፋጠን እንዲቻሉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ጋር ተቀራርቦ መስራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡