null The Ethiopian Broadcast Authority should give attention to digital television technology.

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የዲጂታል ቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ሽግግር እና  የማህበረሰብ ሬድዮ ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን የ6 ወር አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተስፋዬ የዲጂታል ቴሌዥን ቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚመለከት ለሽግግሩ የሚረዳ ረቂቅ አዋጅ፣ የብሮድካስት ኔትወርክ አስተዳደር ድርጅት ማቋቋሚያ ረቂቅ ሕግ እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ በሽግግሩ ዙሪያ የፖሊሲ ውሳኔ በሚሹ ጉዳዮች ላ የውሳኔ ሀሳብን ያካተተ አጭር ማብራሪያ በቦርዱ ውሳኔ መሰረት ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለባለስልጣኑ ቦርድና ለመንግስት መቅረቡን ገልጸው፤ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ የመንግስት ውሳኔ እንዳገኘ ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማህበረሰብ ሬዲዮ ፈቃድን በተመለከተ 48 ጣቢያዎች ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን 31 ጣቢያዎች በስርጭት ላይ እና 17ቱ ስርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በ6 ወሩ 1,176 የብሮድካስት ፕሮግራሞችን ሞኒተር ለማድረግ ታቅዶ 1,228 ፕሮግራሞች ሞኒተር መደረጋቸውን፣ በስድስት ወሩ 11 ቅሬታዎችና ጥቆማዎች የቀረቡ ሲሆን 9ኙ ምላሽ ያገኙ መሆናቸውንና 2ቱ በሂደት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በዋናነት አንስተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ የቀጥታ ኢንተርኔት ኔትወርክ ዝርጋታ እና የሞኒተሪንግ መሳሪያ ተከላ ማድረግ በመቻሉ ተግባራቱን በጥራትና በቅልጥፍና ማከናወኑ፣ በናሙናነት በተመረጡ ፕሮግራሞች ላይ የተሰሩ የሞኒተሪንግ ስራዎች፣ በሳተላይት አማካኝነት የሚሰራው የንግድና ቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ለጠየቁ አመልካቾች በታቀደው መሰረት መፈጸሙንና ሌሎችን ጉዳዮች በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል የዲጂታል ቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በመስክ ምልከታ የተገኙ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መፍትሄ መፈለግ፣ የማህበረሰብ ሬዲዮ ማስፋፋት፣ የውጭ ማስታወቂያ ኢንስፔክሽን ስራን ማጠናከር እና የኦዲት ግኝቶችን በወቅቱ ማረም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡