null The Ethiopian Ethio-Djibouti Railway Project has begun work with US $ 3.8 billion, but it is not going to be the target of its roadblocks.

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መንገድ ፕሮጀክት በ3.8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገንብቶ ስራ የጀመረ ቢሆንም በመስመሩ ላይ በሚያጋጥሙት መስናክሎች ምክንያት የታለመለትን ዓላማ እያሳካ እንዳልሆነ ተገለጸ፣

ይህ የተገለጸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ከለቡ-ደወሌ ባለው 752 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመርና ወደ 8 በሚደርሱ ጣቢያዎች ላይ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ተገኝቶ ለማህበሩ አመራሮች የመስክ ምልከታ ሪፖርቱን ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴው እንዳለው ተቋሙ በተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት የባቡር ጣቢያዎችን አቋቁሞና ሰራተኞችን መድቦ አገልግሎት አሰጣጡ የተሳካ እንዲሆንና ዘርፉ ተመራጭ የትራንፖርት አማራጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት በጥንካሬ አንስቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር በቀጠናው ላለው የህብረተሰብ ክፍል የፈጠረው የስራ እድል ከፍተኛ መሆኑን ያነሳው ቋሚ ኮሚቴው የቻይናን የስራ ባህል ወደ አገራችን ለማምጣትና ቴክኖሎጅውን ለማሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብሏል፡፡

የባቡር ሃዲድ ማሰሪያ ቡለንና ለሌሎች ብረቶች ስርቆት፣ ኮንትሮባንድ ንግድ፣ የደህንነት ስጋትና የደንበኞች መጉላላት እንዳለ በየጣቢያዎቹ በተደረገው ምልከታና ውይይት ማረጋገጡን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ችግሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለይም ከፌደራል ፖሊስና ከጉምሩ ኮሚሽን ጋር ባለው የቅንጅት መላላት በመሆኑ አክሲዮን ማህበሩ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በዚህ ምክንያት የሚበላሸውን የአገር ገጽታና ሊያጋጥም የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መከላከል ይገባዋል ብሏል፡፡

የባቡር መስመሩን ተከትሎ የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ ባለማደጉ ምክንያት ያልተገባ ካሳ ፍለጋ እንሰሳቱን ወደ ባቡር መስመሩ በማስገባት አደጋ እንዲፈጠርና የጸጥታ ችግር እንዲከሰት እያደረገ በመሆኑ የተቋሙ የበላይ አመራሮች እስከታች ድረስ በመውረድ አሰራሩን መፈተሸና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በየደረጃው ያለው አመራር ሃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል ቋሚ ኮሚቴው፡፡

ፕሮጀክቱ ለአገሪቱ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ በከፍተኛ ወጪ ተገንብቶ ስራውን የጀመረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በደረሰበት የግመሎች ግጭት፣ በሃዲዱ ላይ ባጋጠመ ከባድ የጎርፍ አደጋና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በተለይ የሰው መጫኛ ባቡሩ አገልግሎት ማቋረጡን የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው ከአክሲዮን ማህበሩ ባሻገር የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴርና ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት አገልግሎቱ የተሟላ እንዲሆን ማድረግና እንደአገር ተጀመረው የዘርፉ ልማት ወደኋላ እንዳይመለስ ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል በማለት አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ተቋሙ በየጣቢያው ያሉ ሰራተኞች ከደሞዝና ጥቅማጥቅም እንዲሁም ከቋሚ የቅጥር ደብዳቤ አለመድረስ እና ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ የሚያሷቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈትሾ በመፍታት መልካም የስራ አካባቢ መፍጠር ይጠበቅበታል ብሏል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር  የኦፕሬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሾመ እሸቱ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡት አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውንና በተቋሙ አቅም መፈታት ያለባቸውን ለመፍታት እንደሚሰሩ አስታውሰው ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮች ላይ የቋሚ ኮሚቴውን እገዛ እንፈልጋለን ብለዋል   ፡፡

ፕሮጀክቱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስና ሁለት አገር የሚያገናኝ በአፍሪካ የመጀመሪያው ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ያስታወሱት የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ለቴክኖሎጅ ሽግግሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር እንዲሁም የጸጥታ ስጋት የሆኑትን አካባቢዎች ለይተን የኢንዱስትሪውን ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ብለዋል፡፡

በሌላ ዜና ቋሚ ኮሚቴው የአይሻ-ደወሌ 220 ኪሎ ሜትር የክፍያ መንገድና የድርዳዋ-መልካጀብዱ አስፓልት መንገድን ተመልክቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የተጠናቀቁ ቢሆንም ከወሰን ማስከበርና ከኃይል መቆራረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች ስላሉባቸው የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው መስራትና መንገዶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡