null The Federal Attorney general reported 2018 budget performance of 5th month for the House.

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የ2011 በጀት አመት የ5 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ፡፡

ምክር ቤቱ ታህሳስ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግን የ2011 በጀት አመት የ5 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ባቀረቡት ሪፖርት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እና ህብረተሰቡ በፍትህ ስርአቱ ላይ አመኔታ እንዲኖረው እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲከበር ተቋሙ በሰፊው እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የህጎች አተገባበር ላይ ያሉ ቅሬታዎችን ለማሻሻል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ እንዲሁም ህገ ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱም በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩና ህገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን ለፍርድ ከማቅረብ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲብራሩ ሲል ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በምላሹ እንደገለጹት ወንጀል ፈጽመው መደበቅ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ተቁመው በከባድ የሙስና ወንጀል እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደት ላይ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ረገድ ክልሎች የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አስታውሰዋል፡፡

የህግ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ሪፖርቱን አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ያየውን እንዲሁም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያለውን በሰፊው በማብራራት ተቋሙ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የፍትህ ጥማት እና የህግ የበላይነት መከበር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡