null The House approved appointment of the Commissioners.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽነሮችን ሹመት አፀደቀ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 8 ቀን ባደረገው 39ኛ መደበኛ ስብሰባው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች ሹመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ቀርቦለት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ጣሰው ገብሬ ሲሆኑ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው፡፡

የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ካርድናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘ ካቶሊካውያን ሲሆኑ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ ናቸው፡፡

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽነሮች ሹመትን በተመለከተ ኮሚሽኑ ሲቋቋም የነበረው ከህገ መንግስቱና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን ጋር የተያያዘ የተቃውሞ አስተያየት አሁንም በሹመቱ ላይ ዳግም ቀረበ ሲሆን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ኮሚሽኑን ለማቋቋም የሚከለክል ህግ ያለመኖሩንና በወቅቱም የቀረበው ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ መደረጉን አስታውሰው የአሁኑ አስተያየትም የህግ መሰረት የሌለው መሆኑን በመግለፅ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ሹመትን በተመለከተ የተከበሩ አቶ ካሳ ጉግሳ ከብቃትና ከአመራር ጥበብ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከምክር ቤቱ አባላት ተሿሚዎቹ በብቃትና በአመራር ጥበብ ያላቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የማያስገባቸው መሆኑን በመግልፅ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚሽነሮቹ በምክር ቤቱ ሳይሾሙ ስራ በመጀመራቸው ህግ ተጥሷል ተብሎ ለቀረበው አስተያየትም አምባሳደሩ ኮሚሽነሮቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጩ እንጂ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ቢሮ ተመድቦላቸው ስራ ባለመጀመራቸው ምንም የህግ ጥሰት አልተፈጠረም ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡

የሁለቱ ኮሚሽኖች አባላት ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ በመገኘት ቃለ መሐላ ስለፈፀሙ ተሿሚዎቹ ዳግም ቃለ መሐላ መፈፀም እንደማያስፈልጋቸው ተገልፆ በወቅቱ በስራ ምክንያት ቃለ መሐላ ያልፈፀሙት ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ቃለ መሐላውን በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ፈፅመዋል፡፡