null The House approves various proclamations.

ምክር ቤቱ  የተለያዩ አዋጆችን አጽድቋል፡፡

ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ አመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ አዋጆችን አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በእስራኤል መንግስት መካከል በጉምሩክ ጉዳዮች ለመተባበር  በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች እና በገቢዎች ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ  አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የተፈረመው ስምምነት  በእስራኤልና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ፣ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል ፣ ውጤታማ የጉምሩክ አሰራር ስርዓትን ለመዘርጋትና የጉምሩክ ህጎችን በውጤታማነት ለመተግበር የሚያግዝ እንዲሁም ስምምነቱ ከውጭ ጉዳይ ሃገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑ በዝርዝር ተብራርቷል፡፡

ምክር ቤቱ አክሎም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በእስራኤል መንግስት መካከል በቱሪዝም ዘርፍ ለመተባበር በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሴቶች ፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በኩል የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ፤ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ስምምነቱ በእስራኤልና በኢትዮጵያ መካከል የሃገራቱን የቆየ የባህልና የታሪክ ትስስር የሚያጠናክር ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ፣ የሃገራችን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማልማትና ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ስምምነቱ ከሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና ሃገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ  በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በእስራኤል መንግስት መካከል በግብርናው ዘርፍ ለመተባበር በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በግብርና ፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አድምጦ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የትብብር ስምምነቱ የሃገሮቹን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ፣ የሃገራችን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ፣ ልምድ ለመለዋወጥ ፣ የሰው ሃብት አቅምን ለመገንባት እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያተኮረ ስምምነት መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ  የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻልና የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት ለመወሰን የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡

በጉምሩክ ዘርፍ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በመከላከል በገቢው ዘርፍ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ እንደሆነ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አብራርተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል  ጥናት ሲካሄድበት በቆየው የመንግስታት ግንኙነት ረቂቅ አዋጅ ላይም ምክር ቤቱ መክሯል፡፡

 ረቂቅ አዋጁ በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል እንዲሁም በክልል መንግስታት መካከል የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑ ተነግሯል፡፡

እንዲሁም  በፌደራል መንግስትና በክልሎች መካከል ፣ በክልሎች እርስ በእርስ የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ግጭቶች የሚፈቱበትን የግንኙነት  ተቋማዊ ስርዓት መዘርጋት ፣ የግንኙነት ስርዓቱን አፈጻጸምና ውጤታማነት ለማረጋገጥና ለመከታተል የሚያስችል አደረጃጀቶችን፣ አሰራሮችን ፣ መርሆችን መፍጠር ከአላማዋቹ መካከል እንደሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ- ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ጠቅሰዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡