null The House evaluated 6 months performance report of the Ministry of Education.

የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት በዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎች በየደረጃው መቀረፍ እንዳለባቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ ባካሄደው በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የትምህርት ሚኒስቴርን የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አዳምጧል፡፡

በሪፖርቱም የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትን በተመለከተ ስራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመተግበር እና ከህዝቡ የሚነሱ ሀሳቦችን በፖሊሲ ማሻሻያው የሚካተቱ መሆንና አቅም እየገነቡ ለመሄድ ጥቅል ስራው አስከ አምስት ዓመት እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ የቋሙን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ባለፉት ስድስት ወራቶች የመምህራን፣ የርዕሳነ መምህራን እና የሱፐርቫይዘሮችን አቅም ለማጎልበት ዘርፈ-ብዙ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸው ከመምህራን ልማት አንጻር የቅድመ መደበኛና የመሰናዶ መምህራን የአቅርቦት ችግር እንዳለ አብራርተዋል፡፡

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮች ችግሮች ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች በተጋለጡበት ወቅት የአልባሳት እና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት የተማሪ ምደባን፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን፣ የአካቶ ትምህርት እና ለታዳጊ ክልሎች የሚሰጠውን የትምህርት ድጋፍ በተመለከተ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ተማሪዎች የሚመደቡት ባስመዘገቡት ውጤትና በራሳቸው ፍላጎት እንደሆነ ገልጸው የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በዘርፉ  በርካታ ማነቆዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በተመለከተ ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የሰለጠኑና ክህሎት ያላቸው ተዘዋዋሪ መምህራን እንዲያስተምሩ በመደረጉ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በበኩሉ በልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ላይ ውስንነቶች እንዳሉ እና በወላጆች ላይም ክፍተኛ የግንዛቤ ክፍተት እንደሚስተዋልም አንስቷል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የትምህርት ጥራቱን ለማሳደግ፣ የመምህራንን አቅም ለመገንባትና በትምህርት ደረጃ ማሳደግ እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት መስጠት ብቻ የሚያመጣው ለውጥ በቂ ስላልሆነ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩልም የማስተማር ስነ-ዘዴ የሌላቸው መምህራን በዘርፉ መሰማራታቸው በትምርት ጥራት ማስጠበቅ አንጻር አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለውም ጠቁሟል፡፡ የግል ትምርት ቤቶች መንግስት ያወጣውን ስርዓተ ትምህርት እየተከተሉ እንዳልሆነ እና በርካታ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የግል ትምህርት ቤቶች መከፈት በትምህርት ጥራቱ ላይ ሌላ ችግር መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

በትምርት ቤቶች አካባቢ በሚከፈቱ ጫት እና ሺሻ ቤቶች ላይም ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እምዬ ቢተው በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዝግጅት ምዕራፍና የመቶ ቀን እቅድ ማዘጋጀቱን፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ወደ ትግበራ መግባቱን እና ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ መምህራን ስልጠናዎች መሰጠቱን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት፣ ከደረጃ በታች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያለውን የግብዓትና ተያያዥ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸው እንዲሁም በጸጥታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት መካካስ እንዳለበት   አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 22ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤን በሙሉ ድምጽ ፅድቋል፡፡