null The House, in its 24th regular session, heard the 2019 budget 6 months performance report of the Ministry of urban development and construction.

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባው የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን የ2011 በጀት አመት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ከምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ከምክር ቤቱ አባላት እንዲሁም ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ከተነሱት ጥያቄዎችም ህዝቡን የቤት ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን  ከማድረግ ረገድ ከግንባታ መጓተት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ያለበትን የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቅረፍ እና የእጣ አወጣጥ ስርአቱን ከማዘመን አኳያ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተወሰደ ስላለው አፋጣኝ እርምጃ እንዲሁም የህንጻ አዋጅ አተገባበር እና የአከራይ ተከራይ አዋጅንም የሚጨምሩ ናቸው፡፡

በምላሹም የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ እንደገለጹት ለግንባታ መጓተት ምክንቱ የግብአት ዋጋ መጨመር መሆኑን ጠቅሰው የእጣ አወጣጥ ስርአቱን ለማዘመን የሚሰራው ስራም ጊዜ ወስዶብናል ብለዋል፡፡አያይዘውም 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤትን አስመልክቶ 100 ፔርሰንት የቆጠበ ቅድሚያ እድሉን እንደሚያገኝ በመመሪያው የተጠቀሰ መሆኑን አስታውሰው ነገር ግን አሁን የግንባታ ግብአቶች በእጥፍ በመጨመራቸው በመመሪያው የተጠቀሰው መነሻ ዋጋ እንጂ መድረሻ ዋጋ ባለመሆኑ 100 ፔርሰንት ቆጥበናል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ ቦርድ ጉዳዩን እያየው መሆኑን ጠቅሰው የኮንስትራክሽን የዋጋ ንረትን በሚመለከት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የህንጻ አዋጅ አተገባበርን በሚመለከት በሰጡት ምላሽ ግንባታዎች አደጋ እንዳያደርሱ ተሸፍነው እየተሰሩ ቢሆኑም ቅድመ ጥንቃቄ ከማድረግ ረገድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ጉድለቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡ሚኒስቴሩ የአከራይ ተከራይ አዋጂን በሚመለከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተን በቅርቡ ለምክር ቤቱ እናቀርባለንም ብለዋል፡፡

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ በበኩላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበጀት አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን እና ያለበትን የኦዲት ግኝት ለማሻሻል የተሰራውን ስራ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የተመለከተው መሆኑን ጠቅሰው የቤቶች ልማት ጋር ተያይዞ ህዝቡ የተሻለ ምላሽ እየጠበቀ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡አያይዘውም ለሰነድ አልባ ቤቶች ይዞታ የመስጠቱ ስራ ላይ እና ባለቤት አልባ ቤቶችን ከመለየቱ ረገድ ሚኒስቴር መስሪ ቤቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡አክለውም ከብድር አመላለስና አቅርቦት ጋር ተያይዞ አዲስ ለሚገቡ ኢንተርፕራይዞች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡