null The House, in its 30th regular session, heard the 2019 budget 8 months performance report of the Ethiopian National Bank.

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2011 በጀት አመት የ8 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዚ ዶ/ር ይናገር ደሴ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ባንኩ በ8 ወራት ውስጥ ልዩ ልዩ የገንዘብ ፖሊሲዎችን በቅንጅት በመጠቀሙ፣ መንግስት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ከመከተሉም ባሻገር የአገር ወሰጥ ገበያን ለማረጋጋት አንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጦችን ከውጭ አገር ገዝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ  ለህብረተሰቡ ማቅረቡን በመቀጠሉ የአገሪቱ የዋጋ ንረት አምና የካቲት ወር ላይ ከነበረበት 16.0 በመቶ ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት መጨረሻ ወደ 10.9 በመቶ ዝቅ እንዳለገልጸዋል፡፡ 

ለዚህም ዓመታዊ የዋጋ ንረት መቀነስ ዋናው ምክንያተ ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት አምና ከነበረበት 16.4 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ደግሞ ከ15.6 ወደ 11.2 በመቶ በመቀነሳቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 ነገር ግን በአለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ የማንሰራራት አዝማሚያ በማሳየቱ  በአገር ውስጥም የምርትና የአገልግሎቶች አቅርቦትና ፍላጎት ባለመመጣጠኑ የአገሪቱ ዓመታዊ  የዋጋ ንረት ከነጠላ አሃዝ ግብ በላይ ሆኗል ብለዋል፡፡

 በስምንት ወር ውስጥ ባንኩ ከውጭ ለሚገቡ ሸቀጦች በተለይም ለነዳጅ፣ለማዳበሪያና ለመሰረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያ ለሚውሉ ዕቃዎች ግዚ በድምሩ 3.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በብሼራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ በኩል መስጠቱን ገልጸው ሌሎችንም  የተከናወኑ ተግባራት አብራርተዋል፡፡

የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ብሔራዊ ባንክ ጤናማና አስተማማኝ የገንዘብ ስርአት መስፈን ለአገራችን ኢኮኖሚ ወሳኝ በመሆኑ፣ ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ መመሪያዎች በመጠቀም  አሁን ያለውን ችግር ለመፍታትና አገራችን ጤናማና አስተማማኝ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖራት እየተሰራ ያለው ስራ ጥሩ መሆኑን ነገር ግን ክትትልና ቁጥጥሩ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት ገልጿል፡፡

ዘመናዊ  የክፍያ ስርአቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ  መሻሻሉ በጥሩ ጎን አንስቶ፣ የብድር ማስመለስ በሚመለከት የማይመለስ አጠራጣሪ ብድር  ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባና የአነስተኛ ንግድ ተቋማትና ንግድ ባንኮች  ከተቀመጠው ግብ 5 በመቶ በታች መሆኑ ና የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መሆናቸውን አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያለው የማይመለስ ብድር 15 በመቶ የተቀመጠለት ጣሪያ ሲሆን 39.45 በመቶ በመሆኑ ለኪሳራ እየተዳረገ  መሆኑና ብሄራዊ ባንክም የራሱን  አስተዋጽኦ ማድረግ እንደነበረበትና ክትትልና ቁጥጥሩ አናሳ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው እጥረት አንስቷል፡፡

የዋጋ ግሽበትን በሚመለከትም ብሄራዊ ባንክ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት፣ የበጀት አፈጻጸምን በሚመለከት መደበኛው ጥሩ ቢሆንም የካፒታል ወጪ አፈጻጸም በቀጣይ ሊስተካከል እንደሚገባ፣ የገቢና ወጪ ንግድ ላይ ያለው ሰፊ ክፍተት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ከህዝብ እና ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን የባንክ ዋና ገዢ ደ/ር ይናገር ደሴና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ብድር ወስደው ለታለመለት አላማ ያላዋሉ እና ያልመለሱ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጂቶች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

 የዋጋ ግሽፈትን በሚመለከት ወደ እንድ አሃዝ ማውረድ አስቸጋሪ ቢሆንም ግሽፈቱን ለመቆጣጠር ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር ያለበት በመሆኑ የወጪ ንግድ ግብርና እና ማኒፋክቼሪንግ ዘርፉ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡