null The House in its 48th regular session referred different bills to the concerned Standing Committees.

ምክር ቤቱ ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፤ ሁለት ረቂቅ አዋጆችንና አንድ ደንብንም አፅድቋል፡፡

ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ለም/ቤቱ አጭር ማብራሪያ ያቀረቡት ም/አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በአገሪቱ በመከናወን ላይ ካሉ የሪፎርም ስራዎች አንዱ የሆነው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋትና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በየደረጃው እያረጋገጡ መሄድ መሆኑን ጠቁመው የዘመናዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ መገለጫ የሆነው ምርጫና ፓርቲዎች የሚገዙበትን ህግ በአገሪቱ የሚደረጉ ምርጫዎች ነፃ፣ ፍትሀዊና ተዓማኒ ለማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

ረቅቅ አዋጁ በዋናነት የምርጫ ስርአት፣ የምርጫ አፈፃጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትና አስተዳደር፣ የምርጫ ስነ-ምግባር፣ በምርጫ ሂደት የሚነሱ ክርክሮች የሚዳኙበትንና የሚፈቱበትን የአሰራር ስርኣት የያዘ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናጁበት፣ እንደአዲስ የሚዋሀዱበትን ዝርዝር የያዘ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የም/ቤት አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ወቅታዊና በአገሪቱ ለሚታየው ለውጥ አጋዥ መሆኑን ጠቁመው፤ የቀረበበት ጊዜ ግን ረቂቅ አዋጁ በጣም ሰፊ ከመሆኑ እንፃር ቋሚ ኮሚቴዎች በአግባቡ ከማየትና የሚመለከታቸውን አካላት ከማሳተፍ አኳያ እንዴት እንደታየ ማብራሪያ የተጠየቀባቸው ጥያቄዎች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡     

ም/አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ረቂቅ አዋጁ በጣም ሰፊና ወደ ም/ቤቱ ዘግይቶ ቢቀርብም በሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ የታየና ወቅታዊ ከመሆኑ አንፃር የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ የህግ ሂደቱን ጠብቆ ቢመረምረው የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጁ ቁጥር 67/2011 ዓ.ም ሆኖ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ እንዲመራ ለድምጽ አቅርበው ም/ቤቱም በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ መርቶታል፡፡

የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዮሱፍ በሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ከም/ቤት አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

በመቀጠልም የገቢዎች በጀትና፣ ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ለምለም ሀድጎ በገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ እና በህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴዎች የተዘጋጀውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን በማሻሻል የንግድ ስራ እንቅስቃሴን በተቀላጠፈ ሁኔታ በማካሄድ የንግድ ስራን ለማገዝ የሚያስችል መሆኑንም ሰብሳቢዋ አብራርተዋል፡፡

ም/ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ተወያይቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ በሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጽ/ቤት ሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን፤ ሪፖርቱንና የውሳኔ ሀሳቡን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እምዬ ቢተው አቅርበዋል፡፡

ረቂቅ ደንቡ በዋናነት በእውቀት፣ በክህሎትና በልምድ የጎለበቱ ሰራተኞችን ከውጪ ለመሳብና ያሉትንም ለማቆየት የሚያስችል በመሆኑ ም/ቤቱ በህገ-መንግስቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶችንና ግዴታዎች ለመወጣት ያስችለዋል ብለዋል፡፡      

ከም/ቤት አባላትም ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጽ/ቤት ሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ቁጥር 10/2011 ሆኖ በ9 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡