null The House, in its 8th special session, heard the 2019 budget annual report performance reported by Prime Minister H.E. Dr. Abiy Ahmed.

የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ነባር የግጭት መፍቻ መንገዶችን መጠቀም ለአገራችን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፀጥታ መረጋገጥ ዋስትና ናቸው ሲሉ ክቡር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 8ኛ ልዩ ስብሰባው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያቀረቡትን አመታዊ ሪፖርት አዳምጧል፡፡

ሪፖርቱን ያዳመጡት የምክር ቤቱ አባላት የበለጠ መብራራት አለባቸው ያሏቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ጸጥታን የተመለከቱ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፀጥታን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው እንደተናገሩት የመጀመሪያ ስራው ተቋማዊ ሪፎርም ማከናወን ሲሆን በዚህም ሁሉም የጸጥታ፣ የደህንነትና የፍትህ አካላት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት የአሰራር ስርዓትና የአመራር ማሻሻያ ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና አጥፊዎች በህግ እርምት እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም በሰብአዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ቡድኖችና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 48 የሸብር ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር በማዋል የተቃጣው ጥቃት እንዲከሽፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በበጀት አመቱ በትኩረት ከተሰሩ ስራዎች አንዱ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዚህ አኳያ ከመንግስት ጋር ሲዋጉ የነበሩ በርካታ ተቃዋሚዎች ወደ አገራቸው መግባታቸውን፤ዜጎች በምህረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆናቸውን፤ እንዲሁም ከ260 በላይ ሚዲያዎችና ድረ-ገጾች ነፃነነት ማግኘታቸውን አመላክተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ላይ የተፈጸመው ግድያና ስልጣንን በኃይል ለመያዝ በተደረገው  ፍጹም ኋላቀርና አሳፋሪ ድርጊት ማዘናቸውን አንስተው ከዚህ በኋላ ህዝብና መንግስት ተባብረው የህግ የበላይነትን እንደሚያስከብሩና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚደራደር የለውጥ አመራር እንደማይኖር በየትኛውም አካባቢ በግልም ሆነ በቡድን የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዲፕሎማሲ ስራዎች አኳያ የጎረቤት አገራት ሰላም መረጋገጥ ለአገራችንም ከፍተኛ ጥቅም ስላለው ተቀራርበን እየሰራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠናችን ሦስት አህጉራት የሚገኙበትና ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚከናወንበት ቀጠና በመሆኑ ተወዳዳሪነታችንን ለማሳደግና ደህንነታችንን ለመጠበቅ እንዲቻል የባህር ኃይላችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ የእድገት ምጣኔ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሳያ እንደሆነና ይህም ባለፉት ተከታታይ አመታት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የኢኮኖሚ እድገት ለድህነት ቅነሳው ያበረከተው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት ባጋጠሙን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት የእድገት ምጣኔያችን እቀነሰ መጥቷል ብለዋል፡፡

ለማክሮ ኢኮኖሚው መዳከም ዋናው ምክንያት የፋይናንስ ሞዴል አለመኖር በመሆኑ እሱ ሲፈታ አብዛኛው ችግር እንደሚፈታ እንዲሁም  ካለው የስራ አጥ ቁጥር አኳያ የተፈጠረው ስራ ዝቅተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የግሉን ዘርፍ ማጠናከር ችግሩን ለማቃለል ስለሚያስችለን ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ከኑሮ ውድነት አኳያ ዋናው ችግር የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ችግሩን ለማቃለል ከውጭ ስንዴና ዘይት እያስገባ እንደሆነና በቀጣይም ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የመውሰድና የንግድ ሚዛኑን የመጠበቅ ስራዎች እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የአገራችን ህዝቦች በጦርነትና በእርስ በርስ መናቆር ያደገ አገር አለመኖሩን በመገንዘብ፣ ሽብርና ጦርነት ከሚነዙ ተራ አሉባልታዎች በመራቅና ቆም ብለን በማሰብ ያለንን ጉልበት፣ እውቀትና ገንዘብ አሟጠን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለብልግና ልናውለው እና ወደለመድነው ሳይሆን ወደሚያስፈልገን ልንጓዝ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡