null The House of People's Representatives has indicated that the highest public audit institutions have to be accountable.

ከፍተኛ የኦዲት ግኝት የታየባቸው የመንግስት ተቋማት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 41ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት በፌዴራል ዋና ኦዲተር የቀረበውን የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የ2010 በጀት ዓመት የፋይናንስ ህጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፣ እንዲሁም የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

174 የፌዴራል መንገግስት መስሪያ ቤቶች የ2010 በጀት ዓመት የፋይናንስና ህጋዊነትን አስመልክቶ ኦዲት ሲደረጉ በርካታ የሂሳብ አያያዝ ግድፈቶች እና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች እና ህገ-ወጥ አሰራሮችን እንደፈጸሙ በቀረበው ሪፖርት የተገለጸ ሲሆን በሌላ በኩል የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ኦዲት ሲደረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሰመራ እና በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲዎች በድምሩ ከ960 ሺህ ብር በላይ ጉድለት መገኘቱን ምክር ቤቱ መገንዘብ ችሏል፡፡

በተመሳሳይም ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን አስመልክቶ በተደረገው የማጣራት ስራ ክፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በ129 መስሪያ ቤቶችና በ10 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ በወቅቱ ያልተወራረደ 4.2 ቢሊየን ብር መገኘቱን ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን 77 መስሪያ ቤቶችና ሰባት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደግሞ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ያላግባብ 145.6 ሚሊየን ብር ክፍያ መፈጸማቸውን በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ም/ቤቱ አረጋግጧል፡፡

በሌላ በኩል የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ግዥ የፈጸሙ 100 መስሪያ ቤቶች እና ስምንት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሲሆኑ 956.8 ሚሊየን ብር የኦዲት ግኝት የታየባቸው እንደሆነ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አስረድተዋል፡፡

የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት የግዥን አስመልክቶ ተቋማቱ ስራ ለመጀመር የሚያስፈልጓቸውን የኮምፕዩተር፣ የጀነሬተርና መሰል ቁሳቁሶችን ለመግዛት ቢታቀድም ምንም አይነት የእቃ ግዥ ሳይፈጸም ከ67 እስከ 85% ግዥ እንደተፈጸመ ተደርጎ የውሸት ሪፖርት የቀረበ መሆኑን ነው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለምክር ቤቱ የገለጹት፡፡

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ አክለውም ከፍተኛ የኦዲት ጉድለት በሚታይባቸው የመንግስት ተቋማት ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን መስሪያ ቤትን የ2011 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት የመስሪያ ቤቱን ስራዎች በብቃትና በጥራት ለማሳለጥ ሁለንተናዊ ጥረት ቢደረግም ከደመወዝና ከጥቅማጥቅም አንጻር ከፍተኛ የሰው ሀይል ፍልሰት አንደሚስተዋል ነው በሪፖርቱ የቀረበው፡፡     

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ያላግባብ እየባከነ በመሆኑ ከፍተኛ የኦዲት ግኝት በታየባቸው መስሪያ ቤቶች ላይ ተገቢነት ያለው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ገልጸው ይህ ካልሆነ ግን በየጊዜው ሪፖርት ብቻ እያዳመጡ መሄድ የመፍትሄ አካል እንደማይሆን አሳስበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ከፍተኛ የኦዲት ግኝት የታየባቸው የመንግስት ተቋማት ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ የሱፍ የኦዲት ግኝቶች በየዘርፉ ተለይተው መቀመጣቸው ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ አመቺነት እንዳላቸው በጥንካሬነት ያነሱ ሲሆን በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተከናወኑ ተግባራት በእቅድ ክንውን በንፅፅር አለመቅረብ፣ ተቋሙ የህጻናት ማቆያ ግንባታ አለመጀመሩን በክፍተት አስቀምጠዋል፡፡

በመጨረሻም የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 40ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡