null The House claims the youths and sport minister to do more on sporting

ም/ቤቱ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2010 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የእቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የኢፌ.ዴ.ሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅተ እንደገለጹት መንግስት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩልም በበጀት አመቱ ለ2 ሚሊየን 859 ሺህ 900 ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢገኝም በግማሽ አመቱ ለ882 ሺህ 209 ወጣቶች ብቻ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩ አፈጻጸሙምን ዝቅተኛ እንዳደረገው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በስራ እድል ፈጠራ ብቻ ሳይሆን በብድር ስርጭት በኩልም ከተቀመጠው ግብ አኳያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ምክንያቶቹ በአንዳንድ አካባቢዎች አመራሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መጠመድ፣ የአስፈጻሚ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር አናሳ መሆን፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች አቅርቦት መዘግየት፣ ተዘዋዋሪ ፈንድን ለማስተዳደር ከወጣው መመሪያ ውጪ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥና ፈንዱን በፍጥነት በስራ ላይ ያለመዋል በችግርነት እንደሚጠቀሱ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የአገሪቱን የስፖርት ዘርፍ ለማሳድግ ጥረት እየተደረገ ቢገኝም በሁሉም የስፖርት አይነቶች በአህጉር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ለምን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም? ሲል ጥያቄ አንስቷል፡፡  

የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ለምን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም? በሚል የተነሳው ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው ገልጸው፤ በልዩ ልዩ የስፖርት ዘርፎች አገሪቷ ብዙ እምቅ ችሎታ ቢኖራትም በበጀት እጥረትና መሰል ችግሮች በሁሉም ዘርፍ ለመሳተፍ ውስንነት እንደሚስተዋል ገልጸው በተለይ እግር ኳሱን ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ ድጋፎች ቢደረጉም በተለያዩ ምክንያቶች የህዝቡን ስሜት የሚመጥን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡

በሌላ በኩል በዋናነት እንደአገር በአትሌክሱ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በአህጉር እና በአለም ደረጃ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያከሉት፡፡    

የም/ቤት አባላቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጣቶች አደንዛዥ እፅ ከመጠቀም እና በእግር ኳስ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ከሁከትና ብጥብጥ እንዲቆጠቡ መጠነ-ሰፊ ስራዎችን መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእቅድ ዝግጅት ከሰራተኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይቶች ማካሄዱ አንዲሁም ወጣቶች በክረምት መርሀ ግብር ያደረጉትን የበጎ ፈቃድ ስራ በጠንካራ አፈፃጸም እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም በመልካም አስተዳደርና በችግር አፈታት እንዲሁም በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ ግን ከቁጥር በዘለለ በተግባር የተረጋገጠ ስራ መሰራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡