null The House passed by discussing on various proclamation.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል፣

ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ምክር ቤቱ የገቢ፣ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ አዋጆች በሚመለከት ያቀረባቸውን ሪፖርቶችና የውሳኔ ሀሳቦችን አድምጧል፡፡

ከቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ውስጥ የመድን ስራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አንዱ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በመድን ስራ ላይ እንዳይሳተፉ የተጣለው የህግ እገዳ በማንሳት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በመፍቀድ በሀገሪቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጉዞ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ  አዋጁን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

በተመሳሳይ የአነስተኛ ፋይናንስ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች በአነስተኛ ፋይናንስ ስራ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ በሀገሪቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጉዞ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከም/ቤት አባላት ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅሙ እያጎለበተ መጥቷል የሚለው ምንያህል ተጨባጭ ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ናፈቁሽ ደሴ የኢኮኖሚው አቅምና የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅም እያጎለበተ መምጣቱን፣ ይህ ሲባል ግን ክፍተቶች የሉም ማለት እንዳልሆነና እነሱን ለመሙላት የሚያስችሉ የተለያዩ ህጎች እያዘጋጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ም/ቤቱም በአዋጁ ላይ በስፋት ተወያይቶ በሶስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አዋጁን አፅድቋል፡፡

በመቀጠል ም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ መንግስት እና በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ መካከል ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሚመለከት ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ያዳመጠ ሲሆን፤ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የተገኘው ሰማኒያ አምስት ሚሊዮን ዩሮ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች ለመደገፍ የሚውል፣ የ7 አመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ19 አመታት ውስጥ በመካከለኛ ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅና አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት በመሆኑ የወጪ ጫናው ያልበዛ ከሀገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ መካከል ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና በኮሪያ ኤክስፖርት-ኢንፖርት ባንክ መካከል ለደቡብ ብሄራዊ የኤሌትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ስርአት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በማስከተልም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በአረብ ባንክ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት መካከል ለዲላ-ቡሌ-ሃሮ ዋጩ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡