null The House referred a bill to the concerned committee that benefits the country in communication, media and agricultural sectors.

ምክር ቤቱ በ12ኛ መደበኛ ስብሰባው አገሪቱ በኮሙዩኒኬሽን፣ ሚዲያና በግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ የምትሆንበትን የትብብር ስምምነቶች ለቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡  

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ተኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም አካሔዷል፡፡

ም/ቤቱ በዛሬው ውሎ በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መንግስት መካከል በኮሙዩኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽን እና ሚዲያ ዘርፍ የተፈረመውን የትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አዋጅ ቁጥር 15/2011 ሆኖ ለዝርዝር ምርመራ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ግዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው የተመራው ስምምነት ለአገራችን የሚኖረው ፋይዳ፤ በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መንግስት መካከል ያለውን መልካም ወዳጅነትን የበለጠ በማጠናከር  በኮሙዩኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽን እና ሚዲያ ዘርፍ ለአብነትም በአገር ገጽታ ግንባታ፣ በኩነቶች ዝግጅት ፣ በሚዲያ ሰራተኞች አቅም ግንባታ ላይ ልምድና መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል እንዲሁም የጋራ ችግሮችን በመፍታት የአፍሪካዊ ወንድማማችነትን መንፈስ ያጠናክራል ተብሎ ታምኖበት እንደሆነ በስምምነት ሰነዱ መግለጫ ተብራርቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላትም አዋጁ ለምክር ቤቱ ሳይመራ ለምን እንደዘገየ ጥያቄም አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ም/ቤቱ በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መንግስት መካከል በግብርና ዘርፍ ለመተባበር የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 16/2011 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተባባሪነት ለግብርና፣ አርብቶ አደርና የአከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

የስምምነቱ ዓላማም የአገራችንን ዕድገት በማፋጠን በተለይም የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ በማዘመን እና የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር አጋዥ እንደሚሆን ነው የተገለጸው፡፡  

እንደዚሁም ም/ቤቱ ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር የተገኘውን 83.3 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብለት  ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 17/2011 ሆኖ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው በሙሉ ድምጽ ሲሆን የብድሩ አላማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትን በማካሔድ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ኢትዮጵያውያን እና ፈቃድ አግኝተው በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ቁጥራቸው ለተወሰኑ ስደተኞች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ  የታሰበ ፕሮግራም ነው፡፡

በመጨረሻም አስተያየት የሰጡ የምክር ቤቱ አባላትም አሁን ላይ እየተደረጉ ያሉ የብድር ስምምነቶች አገሪቱ ካላት ብድር ዕዳ ሳትወጣ ሌላ በመጨመር ዕዳ እንዲከማች ከማረጉም ባሻገር አገሪቱንም የስደተኞች መናሃሪያ እንዳያደርጋት የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ስምምነቱን በጥልቀት ማጤን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡