null The judiciary system should up hold transparency for protection of citizens’ right.

የዳኞች የፍትህ አሰጣጥ፣ የአሰራር ግልጸኝነት እንዲኖርና በዜጎች ላይ ግፍና በደል እንዳይከሰት ከምክር ቤቱ የሚወከሉ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የህግ ሙያ እና የካበተ ልምድ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባ ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ/ም በተካሄደበት ወቅት ከምክር ቤቱ የሚወከሉ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት ለመመደብ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ለማጽደቅ ለእይታ ቀርቧል፡፡

በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይም ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከምክር ቤቱ የተወከሉ አባላት ስራቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ እና ዜጎች ላይም አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም መቆየቱን ገልጸው፣ አሁን ላይ ለውጡን በሚገባ ለማስቀጠል ከተፈለገ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ለህዝብ እንዲሰሩ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት ከምክር ቤቱ የሚወከሉ ሰዎች ልምድና እውቀቱ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ፣ በዜጎች ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል ዳግሞ እንዳይከሰት የዳኞች የፍትህ አሰጣጥና የአሰራር ግልጸኝነት እንዲኖር እና በቀጣይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቦታው የሚመደቡ የምክር ቤት አባላት የትምህርት ዝግጅታቸውና ሙሉ ማስረጃቸው መታየት እንዳለበት ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡

ከምክር ቤቱ የሚወከሉ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት ለመመደብ የተከበሩ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርኣያ፣ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እና የተከበሩ ወ/ሮ ሰናይት አንዳርጌ ለእጩነት ቀርበዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርኣያ በምክር ቤት አባልነት እንጂ በህግ የትምህርት ዝግጅትም ሆነ ልምድ የሌላቸው በመሆኑ በቦታው ሊመደቡ አይገባም የሚል ተቃውሞ ከምክር ቤት አባላት ቀርቧል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ከምክር ቤት አባላት የተነሱትን ሀሳቦችና አስተያየቶችን አድንቀው በቦታው የሚመደቡ ሰዎች እውቀትና ልምድ ያላቸው ስለመሆኑ በሰፊው አይተናል፤ ሊሰሩ ይችላሉ ብለን አምነንባቸው ነው ለእጩነት ያቀረብናቸው ብለዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ውክልናውን እንደማይቀበሉት ገልጸው፣ በአገሪቱ የፍትህ ስርዓት እንዲነግስ እና በአግባቡ የተቃና ስራ ማከናወን እንዲቻል ምክር ቤቱ የምደባውን ስርዓት እንደገና ማየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበትንና እና የተከበሩ ወ/ሮ ሰናይት አንዳርጌን ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባልነት ምክር ቤቱ በ19 ድምጽ ተአቅቦ፣ በ1 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አሳልፏል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የቀድሞ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን አስመልክቶ ብሄራዊ የሀዘን ቀን ለማወጅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት የክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ስርዓተ ቀብር ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ/ም እንደሚፈጸምና በእለቱም ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በመላ አገሪቱ ዝቅ ብሎ አንደሚውለበለብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልፀዋል፡፡

የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤም ቀርቦ በመሉ ድምጽ ፀድቋል፡፡