null The Meles Zenawi's administration academy has not been able to manage and control.

የመለስ  ዜናዊ  አመራር አካዳሚን  ለመምራትና ለመቆጣጠር  እንዳልተቻለ ተገለጸ ፡፡

ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንንና ተጠሪ ተቋማቱን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ለኮሚሽኑ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ተናግረዋል ፡፡

 ይሁን እንጂ  የአመራር አካዳሚው አመራሮች ለኮሚሽኑ ተጠሪ አይደለንም በማለታቸው ምክንያት ክትትልና ድጋፍ  ለማድረግ እንዲሁም ለመቆጣጠር እንደተቸገሩ የኮሚሽኑን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኮሚሽኑንና ተጠሪ ተቋማቱን ሪፖርት ሲገመግም የአመራር አካዳሚው የስራ ኃላፊዎች እንዳልተገኙ ኮሚሽነሩ ተናረው ፤ ጉዳዩንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሳወቁና እየታየ እንደሆነ  ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የኢህአዴግን ልማታዊ ዴሞክራሲዊ መንግስት መስመርን  የተከተለ በመሆኑ በተቀመጠው አሰራር መሰረት ለመገምገምና ለመምራት እንደተቸገሩ ቢገልጹም ፤ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የኢህአዴግ ተቋም አይደለም በአዋጅ የመንግስት ተቋም ሆኖ ነው የተደራጀው ሲሉ የፐብሊክ ሰርቪስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ማዘንጊያ ኢያቶ አብራርተዋል፡፡

 እስከየት ድረስ መሄድ እንዳለባችሁ ለይታችሁ በተለይም ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጋችሁ ብትሰሩ ሲሉ አቶ ማዘንጊያ አክለዋል፡፡

የ 2011 በጀት አመትን እቅድ በመከለስ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ወደ ተግባር መገባቱ ፣ ተጠሪ ተቋማት ላይ ያሉ ችግሮችን በጥናት በመለየትና ችግር ያለባቸው አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱ ፣ በፍኖተ ካርታ ላይ ጥናቶችንና ወርክሾፖችን ማዘጋጀት መቻሉ ፣  ውስጣዊና ውጫዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተለይተው  በተለይም ከስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎች መፈታታቸው ፣ ከጀኔራል ኦዲተር ጋር ተያይዞ ተስተውለው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እስከ 18 ሚሊዮን  የሚደርስ ብር እንዲወራረድና እንዲሰረዝ መደረጉ  ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

በሌላ በኩል ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ በቀጣይ ሊኖሩ በሚችሉ የለውጥ ስራዎች የአተገባበር አቅጣጫ ሰነድ ዝግጅት መዘግየት መኖሩ ፣ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ትግበራ /JEG/ ለረጅም አመታት መጓተቱ ፣  የሰው ሃብት ህጎች አፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር ተደራሽነት በቂ አለመሆኑ ፣ በፌደራል መንግስት ተቋማት የሰራተኞች ብሄራዊ ተዋጽኦ የማመጣጠን ስራ በስትራቴጅክ እቅድ ቢታቀድም ውስንነት መኖሩ ፣ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝና አሰራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት አንስቷል፡፡

በስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን /JEG/ ዓላማ አስፈላጊነትና ምንነት ያሉ የግንዛቤ እጥረቶችን እንዲሁም በአሰራር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት ኮሚሽኑ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ እንዳለበት አቶ ማዘንጊያ አሳስበዋል፡፡

 የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው በኩል በእጥረት የታዩ አፈጻጸሞችን በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡