null The Mining Trading darft bill endorsed.

የማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ፡፡

ረቂቅ አዋጁ በተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርመራ ሲደረግበት ቆይቶ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ምክር ቤቱ ባደረገው 39ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በአጀንዳነት ቀርቦ አዋጅ ቁጥር 1144/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡

ነባሩ የማዕድን ግብይት አዋጅ በአዲስ እንዲተካ ያስፈለጉ ጉዳዮችን ቋሚ ኮሚቴው ለማመላከት ሞክሯል፡፡ ባለፈቃዶች አሁን ፈቃድ የሚያገኙት በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ መስተዳድሮች ይሆናል፡፡ በፌዴራል መንግስት በውክልና ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ፈቃዶች ቀርተዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ማዕድናት ባሉበት አካባቢና በተግባር ስራውን ሊሰራ በሚችል አካል ፈቃዱ ሊሰጥ ይገባል የሚል አቋም አራምዷል፡፡

ሌላው፤ የከበሩ ማዕድናት የላኪነት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የወሰደ ሰው ያለገደብ ሁሉንም አይነት የከበሩ ማዕድናት ወደውጭ መላክ በመቻሉ ስራውን በውስን ሰዎች ብቻ በማሰራቱ ለሌሎች ዜጎች የስራ ዕድል አይከፍትም ነበር ያለው ቋሚ ኮሚቴው አሁን የሚሰጠው ፈቃድና የብቃት የምስክር ወረቀት በማዕድን ዓይነቱ ተለይቶ እንዲሰጥ ስለሚያደርግ ለዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም አመልክቷል፡፡

የአሁኑ አዋጅ የግብይት ፈቃዱ ሁሉንም የማዕድናት አይነቶች ማካተቱን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሞ ህገ ወጥ የማዕድናት ዝውውር ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ላይም አስተማሪ ቅጣት እንደሚጥልም በማመልከት የተደረገው የህግ ማሻሻያ ጠንካራ ምክንያቶች እንደነበሩት ለመጠቆም ሞክሯል፡፡

የተሰጠ ፈቃድ እንዴት እንደሚሰረዝና የፈቃድ ሰጪው አካል ስልጣንና ተግባር ምን መምሰል እንዳለበት በረቂቅ አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ጉድለት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው በምርመራው ወቅት በማግኘት የራሱን ማሻሻያዎች በማቅረብ በምክር ቤቱ እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነት በአዋጁ ቦታ እንዲያገኝ አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ሪፖርቱንና የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የተከበሩ ወ/ሮ ጀምበርነሽ ክንፉ የማዕድናት ግብይት አዋጅ ዕቃ የመግዛትና የመሸጥ ዓይነት በመሆኑ የቀረቡትን አስተያየቶች እንደማያስተናግድ በመግለፅ አስተያየቶቹ በማዕድን ስራዎች አዋጅ እንደሚሸፈኑ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡